ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያን የኒውክሌር ማስፈራሪያ ለማስቆም ዓለም እርምጃ መውሰድ አለበት - ዜሌንስኪ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የሩሲያ ባለሥልጣናት የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ለመጠቀም የራሳቸውን ማኅበረሰብ ማዘጋጀት መጀመራቸውን ገለጹ።
ነገር ግን ዜሌንስኪ ሩሲያ እነዚህን የጦር መሣሪያዎች ትጠቀማለች የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ፣ በሩሲያ ላይ ጥቃት ለመፈፀም አስጠንቅቀዋል መባላቸውን ያስተባበሉ ሲሆን፣ ቀደም ብሎ የሰጡት አስተያየት በተሳሳተ መልኩ የተተረጎመ መሆኑን አስረድተዋል።
ዜሌንስኪ ለሩሲያ የኒውክሌር ስጋት “መጀመሪያ የመከላከያ እርምጃዎችን መጠቀም አለብን” በማለት ማዕቀቦችን የጠቀሱ ሲሆን “ጥቃት ግን አማራጭ መሆን የለበትም” ብለዋል።
ይሁን እንጂ በቅርብ ሳምንታት የዩክሬን ጦር በፈፀመው መልሶ ማጥቃት ሰፊ ቦታዎችን መቆጣጠር ችሏል። ይህም የሩሲያ ኃይሎች ለረዥም ጊዜ ተቆጣጥረውት የቆዩትን ቦታ ጥለው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አራት የዩክሬን ግዛቶችን ወደ ሩሲያ በከፊል ማጠቃለላቸውም ሞስኮ ለሽንፈቷ የሰጠችው ምላሽ ነው ብላለች ኪዬቭ።
ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን ወደ ራሷ ማጠቃለሏ ሕገ ወጥ ነው በሚል በስፋት ውድቅ የተደረገ ሲሆን፣ ከተቀሰቀሰ ሰባት ወራትን ያስቆጠረውን ጦርነት ይበልጥ እንዳያባብሰው ስጋት ፈጥሯል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ሌሎች ከፍተኛ የሩሲያ ባለሥልጣናትም እነዚህን ቦታዎች ለመከላከል አነስተኛ እና ስልታዊ የሆኑ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ የምዕራብ አገራት ባለሥልጣናት ሞስኮ ይህንን መሣሪያ ለመጠቀም እየተዘጋጀች መሆኑን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ኪዬቭ በሚገኘው የፕሬዝዳንት ቢሮ ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የሩሲያ ባለሥልጣናት ማኅበረሰባቸውን ማዘጋጀት ጀምረዋል። ይህ ደግሞ አደገኛ ነው። በእርግጥ ኒውክሌር ለመጠቀም ዝግጁ አይደሉም፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መነጋገር ጀምረዋል። ይጠቀሙት አይጠቀሙት እነርሱም አያውቁም። እኔ እንደማስበው ግን መናገራቸው በራሱ አደገኛ ነው” ብለዋል።
ጨምረውም “አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት የኒውክሌር መሣሪያ ይጠቀማሉ የሚለው እርግጠኛ አይደለም ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ከተጠቀሙ በኋላ ለአገሪቷ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ስብዕናም ምንም የሚያገኙበት ነገር እንደሌለ ስለሚረዱ ነው” ሲሉ ምክንያታቸውን አስረድተዋል።
ሆኖም ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ሐሙስ ዕለት በበይነ መረብ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ በሩሲያ ላይ ጥቃት እንዲፈፀም ጥሪ ማቅረባቸው የተነገረ ሲሆን፤ እርሳቸው ግን “የተጠቀምኩት የዩክሬን ቃል ከአውድ ውጪ ተወስዷል” ሲሉ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።
ዜሌንስኪ ቀደም ብለው የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “ይህ ሌላ የዓለም ጦርነት እንዲጀመር መማጸን ነው” ሲሉ አውግዘውታል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭም፣ የዜሌንስኪን አስተያየት “ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት መጀመሯ ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ነው” ብለውታል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በበኩላቸው “እነሱ [ሩሲያውያን] ንግግሩን በሌላ መልኩ በመተርጎም ለራሳቸው በሚጠቅማቸው መልኩ በራሳቸው መንገድ ተረድተውታል” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዜሌንስኪ ጋር ቃለ ምልልስ የተደረገው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ ሩሲያ ኒውክሌር ትጠቀማለች የሚለው ስጋት በቀዝቃዛው ጦርት ወቅት ከነበረው የኩባ የሚሳኤል ቀውስ ወዲህ ከፍተኛ የኒውክሌር ስጋት ያየለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ካሉ በኋላ ነው።
ይህንን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ አሁን ላይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፣ የሩሲያ ዛቻ ለዓለምም አደጋ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
ሞስኮ በአውሮፓ ትልቅ የሆነውንና ፕሬዝዳንት ፑቲን የራሳቸውን ንብረት ለማድረግ እየሞከሩ ያሉትን የኒውክሌር ጣቢያ ዛፖሪዢያን በመቆጣጠር እርምጃዋን ጀምራለች ሲሉም ከሰዋል።
በኒውክሌር ጣቢያው ምንም እንኳን ዩክሬናውያን ሠራተኞች ቢሰሩም በሥፍራው ወደ 500 የሚጠጉ የሩሲያ ወታደሮች እንደሚገኙ ዜሌንስኪ ተናግረዋል።
“ዓለም የሩሲያን ኃይሎች ድርጊት ማስቆም ይችላል” ያሉት ዜሌንስኪ “የሩሲያ ኃይሎች የኒውክሌር ጣቢያውን ለቀው እንዲወጡ ዓለም ማዕቀቡን ተግባራዊ ማድረግ ይችላል” ብለዋል።
በምዕራባውያኑ በተራቀቁ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ድጋፍ የተደረገለት የዩክሬን ጦር በምሥራቅ እና በደቡብ የአገሪቷ ክፍል ባደረጋቸው ትግሎች፣ ክሬሚሊን የሩሲያ ክፍል ነው በምትለው አካባቢዎች ጭምር የሚገኙ ከተሞችን እና መንደሮችን ተቆጣጥሯል።
የሩሲያ ጦር ውድቀትም ለፕሬዝዳንት ፑቲን አሳፋሪ፣ ለአገሪቷ ጦር ደግሞ ያልተለመደ ትችትን አስከትሏል።
በዚህ መካከልም ፕሬዝዳንት ፑቲን በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠባባቂ ኃይሎች እያሰባሰቡ እንደሆነ አስታውቀዋል። ይህም በሩሲያ ውስጥ ፀረ ጦርነት ተቃውሞ እንዲፈጠር ያደረገ ሲሆን፣ ለውትድርና ብቁ በሆነ እድሜ ላይ ያሉ በርካታ ወንዶችንም ለስደት ዳርጓል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ሩሲያ ሕጻናትን ጭምር በጦርነቱ እያሳተፈች እንደሆነ በመጥቀስ “ህጻናቱ የሚመጡት ባዶ እጃቸውን ያለ መሳሪያ እና ትጥቅ ነው” ብለዋል።
“ፑቲን የሚፈራው የኒውክሌር ጥቃት አይደለም፤ የሚፈራው የራሱን ማኅበረሰብ ነው። ሕዝቦቹን ይፈራል ምክንያቱም እርሱን ሊተኩ የሚችሉት እነርሱ ብቻ ናቸው። ሥልጣኑን ነጥቀው ለሌላ ሰው መስጠት የሚችሉት እነሱ ናቸው” ሲሉም አክለዋል።
በመጨረሻ ዩክሬን በጦርነቱ ብታሸንፍ ፕሬዝዳንት ፑቲን መትረፍ ይችሉ እንደሁ የተጠየቁት ዘሌንስኪ “እሱ ምንም ግድ አይሰጠኝም” ሲሉ መልሰዋል።