ብራዚላዊቷ ‘አዋቂ’ በመጠቀም እናቷን 140 ሚሊዮን ዶላር ማጭበርበሯን ፖሊስ አስታወቀ

ታትሟል

በብራዚል የምትኖር አንዲት ግለሰብ ‘አዋቂ’ በመጠቀም እናቷን ከስነ-ጥበብ ስራዎችና  ጌጣጌጥ 140 ሚሊዮን ዶላር ማጭበርበሯን ፖሊስ አስታወቀ።

ይህ ማጭበርበር የተፈጸመባት በብራዚል ግንባር ቀደም የሆነው የጥበብ ስራዎች ሰብሳቢ ባለቤት ናት።

ልጇ የስነ ጥበብ ስራዎቹ የተረገሙ እንደሆኑ ለማስመሰል ‘አዋቂ’ ወይም ሳይኪክ ተጠቅማለች በሚል የማጭበርበር ተግባር ፈጽማለች ተብሏል።

በብራዚል ታዋቂ ከሆኑት አርቲስቶች መካከል የአንደኛው ስዕል ከአልጋ ስር ተደብቆ መገኘቱ ተዘግቧል።

የሪዮ ዴጄኔሮ ፖሊስ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ ማጭበርበሩ የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2020 እንደሆነ ነው።

 ማጭበርበር የተፈጸመባት ግለሰብ ልጅዋ እንደታመመች እና ለህክምና እንድትከፍልም አዋቂ (ሳይኪክ) በተባለው ግለሰብ ተነግሯታል ተብሏታል።

በቀጣዮቹ ወራቶች ውስጥ ልጇ እና አዋቂ የተባለው ግለሰብ ሥዕሎቹ የተረገሙ ናቸው በማለት የተጠናወታቸውን መንፈስ ለማስወገድ መጸለይ አለበት በሚል የስነ ጥበብ ስራዎቹን ከቤት መውሰድ እንደጀመሩ ፖሊስ ተናግሯል።

ይህ የማጭበርበር እቅድ በርካታ ተባባሪዎችን ያሳተፈ መሆኑን ፖሊስ በምርመራ ደርሼበታለሁ ብሏል።

ልጅቷ እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች እናቲቷን ለወራት ቤት በማቆየት በደል ፈጽመውባታል ተብሏል።

የታዋቂ ብራዚላውያን አርቲስቶች ስራዎችን ጨምሮ "16 ሥዕሎችን ወስደዋል” ሲሉ የፖሊስ ኃላፊ ጊልቤርቶ ሪቤሮ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ታርሲላ ዶ አማራል የተሰኘው ታዋቂው የብራዚል ሞደርኒስት (ዘመናዊ) ሰዓሊ ስራዎች የሆኑ ሶስት ስዕሎች ተሰርቀዋል የነዚህም ስራዎች ዋጋ 137.69 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ፖሊስ ግምቱን አስቀምጧል።

ከነዚህም ስራዎች ውስጥ ‘ሶል ፖዬንቴ’ ስያሜ የተሰጠው ስራ ከተጠርጣሪዋ አልጋ ሥር መገኘቱን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ገልጸው፣ ሌሎች ሥራዎች ደግሞ ለሥዕል ጋለሪዎች ተሽጠዋል ተብሏል።

ፖሊስ ለዓመታት በዘለቀው ወንጀል ሰባት ሰዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በገንዘብ ማጭበርበር፣ ዝርፊያ፣ ቅሚያ፣ የሀሰት እስራት እና በተባበረ ወንጀል  ክስ እንደሚመሰረትባቸው ሮይተርስ ዘግቧል።