የሆሊውድ የፊልም ባለሙያዎች አድማ ለወራት ሊቆይ እንደሚችል ተነገረ

ታትሟል

ከ160 ሺህ በላይ የሆሊውድ የፊልም ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል የተባለው የሥራ ማቆም አድማ እስከ መጪው ዓመት ታኅሳስ ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ተነገረ።

በፊልሙ ኢንዱስትሪ ውስጥ ስመ ጥር የሆኑት ጄሰን ሱዴይኪስ፣ ሱዛን ሳራንደን እና ሌሎች ታዋቂ ተዋንያን በሆሊውድ ውሰጥ በስድስት አስርት ዓመታት ታይቶ አይታወቅም የተባለውን አድማ ተቀላቅለዋል።

በዚህ አድማው ወቅት ተዋናዮች በፊልሞች ላይ አይተውኑም፣ ፊልሞችንም አያስተዋዉቁም።

የአቫታር እና ግላዲያተር ተከታይ ፊልሞችን ጨምሮ በርካታ በመሰራት ላይ ያሉ ዋና ዋና ፊልሞች በዚህ አድማም ሊቆሙ እንደሚችሉም ተነግሯል።

የፊልም ጸሐፊዎች በግንቦት ወር ላይ የሥራ ማቆም አድማ የመቱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ ተቀላቅለዋቸዋል።

የሆሊውድ ጸሐፊዎችና ተዋናዮች ይህንን አድማ ለመምታት ዋነኛ ምክንያት የሆናቸው ክፍያ፣ የሥራ ሁኔታ እና በፊልሞች ላይ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) መጠቀም የፈጠረው ስጋት ናቸው።

በኤችቢኦ ላይ በሚታየው ተከታታይ ፊልም ‘ሰክሰሽን’ ዋና ተዋናይ ሆኖ የሚጫወተው ብራያን ኮክስ ለቢቢሲ እንደተናገረው የሥራ ማቆም አድማው እስከ አውሮፓውያኑ የዓመቱ መጨረሻ ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ነው።

“ የፊልም ማሰራጫ ሁኔታዎች ኢንዱስትሪውን ሙሉ በሙሉ እንደቀየረው” ተዋናዩ ተናግሯል።

“በፊልም ማሰራጫ ጣቢያዎች ላይ ከፍተኛ ገንዘብ እየተተረፈ ባለበት ሁኔታ ጸሐፊዎቹ እና ተዋናዮቹን ከዚህ ጨዋታ ውጭ አድርገው ሊበዘብዙን ነው የሚፈልጉት” ብሏል።

ከፊልም ስቱዲየዎች እና ከማሰራጫ ጣቢያዎች ጋር ሐሙስ ሊደረግ የነበረው አዲስ የውል ስምምነትም ከሽፏል።

የፊልም ተዋንያኖች ማኅበር የሆነው (ኤስኤጂ) አሊያንስ ኦፍ ሞሺን ፒክቸር እና ቴሌቪዥን ፕሮዲውሰርስ የተባሉት ስቱዲዮዎች “ፍትሃዊ ውል” ለማቅረብ ፈቃደኛ አልሆኑም ሲሉ ክሳቸውን አቅርበዋል።

ወደ 160 ሺህ የሚጠጉ ተዋናዮችም በዚያችው ቀን እኩለ ሌሊት ላይ ሥራ አቋርጠው ወጥተዋል። ከዚህ ቀደም የሥራ ማቆም አድማ የመቱትን 11 ሺህ 500 የሚሆኑት የአሜሪካ ጸሐፊዎች ማኅበር አባላትም ተቀላቅለዋል።