ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊባኖስ ውስጥ ከወቅት ጋር በሚደረገው የሰዓት ለውጥ ምክንያት አለመግባባት ተፈጠረ
ሊባኖስ ውስጥ ከወቅት ጋር ተያያዞ በሚደረገው የሰዓት አቆጣጠር ለውጥ ምክንያት በሁለት ተቃራኒ የሰዓት ቀጠናዎች ምክንያት ውዝግብ ተፈጥሯል።
ቀዝቃዛው ወቅት እያበቃ ሞቃቱ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት የሊባኖስ ፖለቲከኞች እና የሃይማኖት መሪዎች ተቃራኒ የሆኑ የሰዓት አቆጣጠር ተግባራዊ እንዲሆን በመፈለጋቸው መግባባት አልቻሉም።
የአገሪቱ ባለአደራ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ናጂብ ሚካቲ ጾም ላይ ያሉ ሙስሊሞች ተጨማሪ የጾም ሰዓት እንዳይጨመርባቸው አዲሱ የሰዓት አቆጣጠር በረመዳን ጾም ማብቂያ ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን አሳውቀዋል።
ነገር ግን የአገሪቱ ክርስቲያን ባለሥልጣናት ደግሞ በየዓመቱ እንደሚደረገው የሰዓት አቆጣጠር ቅያሪው የአውሮፓውያኑ የመጋቢት ወር የመጨረሻ እሁድ በሆነው በዛሬው ዕለት እንዲጀምር አድርገዋል።
በርካታ ተቋማትም ይህንን የሰዓት አቆጣጠር ቅያሪን እንደሚከተሉ ተነግሯል።
በዚህም ሳቢያ በአገሪቱ ውስጥ ለቀጣይ ሳምንታት ሁለት የሰዓት አቆጣጠር ሊኖር እንደሚችል እና ግራ መጋባት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ይህ አለመግባባበት ለዘመናት በአገሪቱ የቆየውን ፖለቲካዊ ወሳኔዎች በሃይማኖት ቡድኖች መካከል ክፍፍል የማስከተሉ ሁኔታ አሁንም መቀጠሉን ያሳያል ተብሏል።
በ1970ዎቹ ማብቂያ እና በ1980ዎቹ ውስጥ ሊባኖስ በክርስቲያን እና በሙስሊም አንጃዎች መካከል በተፈጠረ ጥልቅ መከፋፈል የተነሳ ለዓመታት የቆየ የእርስ በርስ ጦርነት መካሄዱ ይታወሳል።
ሱኒ ሙስሊም የሆኑት የአገሪቱ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ የሰዓት ለውጡ ከአራት ሳምንታት በኋላ ሚያዚያ 12/2015 ዓ.ም. ላይ እንዲጀምር ባለፈው ሐሙስ ውሳኔያቸውን አሳውቀው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ውሳኔያቸው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይገልጹም፣ ታዛቢዎች ግን በሙስሊሞች የረመዳን ጾም ወቅት ያላቸውን ድጋፍ ከፍ ለማድረግ ነው ይላሉ።
ከቀናት በፊት የጀመረው የረመዳን ጾም ሚያዚያ 13 እንደሚያበቃ ይጠበቃል።
ከወቅት ጋር የሚደረገው የሰዓት ለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሳይደረግ ከቆየ፣ በጾም ላይ የሚገኙት የእስልምና እምነት ተከታዮች አንድ ሰዓት ቀደም ብለው ጾማቸውን ይድፋሉ።
ለውጡ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ግን አንድ ሰዓት ዘግይተው ያፈጥራሉ ማለት ነው።
በሊባኖስ ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላት የክርስቲያን ማሮናይት ቤተክርስቲያን ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ “ያልተጠበቀ ነው” በማለት እንደማትቀበለው ገልጻለች።
በርካታ የሊባኖስ ታላላቅ ድርጅቶችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ እንደማይስማሙበት በመግለጽ ችላ ብለውታል። በዚህም በአገሪቱ ያሉ ሁለት የዜና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ሰዓታቸውን ከዛሬ ጀምሮ አስተካክለዋል።
የአገሪቱ አየር መንገድ የሆነው ሚድል ኢስት አየር መንገድ ግን ሁለቱንም የሚያካትት እርምጃ ወስዷል። የአየር መንገዱ ሰዓት እና የመገልገያዎቹ ሰዓቶች ለውጥ ሳይደረግባቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ መሠረት ይቆያሉ።
የዓለም አቀፍ የበረራ ፕሮግራሞቹ እንዳይዛቡ ደግሞ ሰዓቱን ከቀሪው ዓለም ጋር ተመሳሳይ በማድረግ ለውጥ እንደሚያደርግ አሳውቋል።