ለቀናት ሲፈለግ የነበረው "ተአምረኛ" የተባለው የአንድ ዓመት ጨቅላ ከመንገድ ዳር በሕይወት ተገኘ

ሉውዚያና የሚገኘው አውራ ጎዳና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአሜሪካዋ ሉዊዚያና ግዛት ለቀናት ሲፈለግ የነበረ የአንድ ዓመት ጨቅላ ከአንድ አውራ ጎዳና አጠገብ ሳር ውስጥ ሲድህ መገኘቱ ተገለጸ።

ለሁለት ቀናት ምግብ እና ውሃ ሳያገኝ የቆየው ጨቅላ የተገኘው አንድ የከባድ መኪና ሹፌር ሕጻኑን ሳር ውስጥ ዳዴ ሲል ከተመለከተው በኋላ ነው።

የፖሊስ መኮንን ጋሪ ጊሎሪ ሕፃኑ “ውሃና ምግብ ሳይቀምስ ለሁለት ቀናት ከቤት ውጭ ብቻውን ቆይቶ በሕይወት መትረፉ ተአምር ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፖሊስ ይህን ጨቅላ መፈለግ የጀመረው የሕጻኑ ታላቅ ወንድም የሆነ የአራት ዓመት ልጅ በአቅራቢያው በሚገኝ ኩሬ ውስጥ ሞቶ ከተገኘ በኋላ ነው።

የአራት ዓመቱ ልጅ ሞት እና የአንድ ዓመቱ ጨቅላ የመጥፋት ዜና በርካታ አሜሪካውያንን አስደንግጦ ነበር።

የሁለቱ ልጆች መጥፋትን ተከትሎ ክስተቱ ካጋጠመበት ሉዊዚያና በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ሚሲሲፒ የነበረችው የልጆቹ እናት አሊያህ ጃክ በቁጥጥር ስር እንድትውል ተደርጓል።

ጃክ አሁን ላይ ሚሲሲፒ በእስር ላይ የምትገኝ ሲሆን የጠፉ ልጆቿን በተመለከተ ሪፖርት ባለማድረጓ ወደ ሉዊዚያና ተላልፋ በመሰጠት ጉዳዩዋ እንዲታይ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።

ተጨማሪ የክስ መዝገቦች ሊከፈቱባት እንደሚችሉ ፖሊስ አስታውቋል።

ለሁለት ቀናት የሚበላው እና የሚጠጣው ሳያገኝ የቆየው ሕፃኑ፤ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ረቡዕ ዕለት ሕጻናት ጥበቃ አገልግሎት እንዲቀላቀል ተደርጓል።

“ተአምረኛው ሕፃን ብለን እንጠራዋለን” ሲሉ ፖሊስ መኮንኑ ተናግረዋል።

"መላ ሰውነቱ ላይ የነፍሳት ንክሻ ቢያጋጥመውም ጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።"

የአየር ሁኔታው እንደረዳቸውም የፖሊስ መኮንኑ ተናግረዋል።

የሉዊዚያና ከባድ የበጋ የአየር ሁኔታን በመጥቀስ "ፀሐይ ወጥታ አየሩን አላሞቀችውም" ብለዋል።