ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዲሞክራቲክ ኮንጎ አማጺያን እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች 45 ሰዎችን ገደሉ
ባለፈው ሳምንት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሰሜን ኪቩ ግዛት በደረሱ ጥቃቶች ቢያንስ 45 ሰላማዊ ዜጎች ተገደሉ።
በወርቅና በተለያዩ ማዕድናት ምክንያት በታጣቂ ቡድኖች መካከል ለአስርት ዓመታት የዘለቀው ውጊያ አካባቢውን ከማውደሙ በተጨማሪ ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።
የኮንጐ መንግሥት የዚህ ሳምንቱ ግድያ በማን እንደተፈጸመ ይፋ አላደረገም።
በርካታ የአገር ውስጥ ምንጮች ግን ተጠያቂው ከኢስላሚክ ስቴት ጋር ግንኙነት ያለው አላይድ ዲሞክራቲክ ፎርስስ (ኤዲኤፍ) እንደሆነ ተናግረዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በቤኒ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ በርካታ መንደሮች ውስጥ ሲሆን ጥቃቱን ተከትሎም በርካታ ሰዎች ከአካባቢው ሸሽተዋል ተብሏል።
የከፋ አደጋ የደረሰበት ማሞቭ የሚባለው ወረዳ እንደሆነ ዘገባዎች ጠቁመዋል። በወረዳዋ በርካታ ቤቶች ከመቃጠላቸውም በላይ ሞተር ሳይክሎች ተዘርፈዋል።
የቤኒ የአስተዳዳሪ የሆኑት ሊዮን ሲቪዌ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት “ጉዳት የደረሰባቸውን የማፈላለጉ ሥራ በመቀጠሉ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል። ህዝቡ ደህንነቱ የተጠበቀ ወደሚባሉ አካባቢዎች እየሸሸ ነው።”
ኤዲኤፍ በ1990ዎቹ በምስራቅ ዩጋንዳ ድንበር አቅራቢያ የተቋቋመ ሲሆን አገሪቱን ለረዥም ጊዜ የመሩት የፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ መንግስት በሙስሊሞች ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በመቃወም መሳሪያ እንዳነሳ ይነገራል።
ከኢስላሚክ ስቴት ጋር ያለው ጥምረት የጀመረው ከስድስት ዓመታት በፊት ነው ተብሎ ቢታሰብም ተንታኞች ግንኙነቶቹ ጠንካራ አይደሉም ይላሉ።
ኢስላሚክ ስቴት በበይነ መረብ ይፋ እንዳረገው በሰሜን ኪቩ ከተፈጸሙት ጥቃቶች አንዱ በክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠረ ነው ብሏል።
በ2021 የኡጋንዳ እና የኮንጐ ሃይሎች በኤዲኤፍ አማጽያን ላይ የጀመሩት የጋራ ወታደራዊ ዘመቻ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ማስቆም አልቻለም።
ኤም 23 የተባለው ሌላኛው አማጺ ቡድን በቅርቡ በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የጀመረው ዘመቻ እየጨመረ አንዳንድ አካባቢዎችንም ከመንግስት ሃይሎች እየተቆጣጠረ ይገኛል።
ሩዋንዳ የኤም 23 አማጺያንን እንደምትደግፍ በሰፊው ቢገለጽም ኪጋሊ ግን ይህንን አጥብቃ ታስተባብላለች።