ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመጀመሪያው አጭር የጽሁፍ መልዕክት ከተላከ 30 ዓመት ሞላው
ባለንበት ዘመን ከፈጣን የግንኙነት ዘዴዎች መካከል አንዱ የሆነው የአጭር ጽሁፍ (ቴክስት) መልዕክት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሞባይል ስልክ የተላላፈው የዛሬ 30 ዓመት ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ ነበር።
በዚህም ልክ የዛሬ 30 ዓመት የሞባይል ስልክ አገልግሎት አቅራቢው ቮዳፎን ኢንጂነር በርክሻየር ውስጥ ለሙከራ የላከው አጭር የጽሁፍ ምልዕክት የመጀመሪያው ሆኗል።
የመጀመሪያው የሙከራ መልዕክትም “መልካም ገና” [ሜሪ ክሪስመስ] የሚል ነበር።
ኒሊ ፓፕዎርዝ የተባለው ሠራተኛ ከኩባንያው ኃላፊዎቹ አንዱ ለነበረው ሪቻርድ ጃርቪስ ገናን እያከበረ በነበረበት ወቅት መልዕክቱን የላከለት ሲሆን፣ ምላሽ ግን አላገኘም ነበር።
ጃርቪስ በወቅቱ ይዞ የነበረው ስልክ ለገበያው አዲስ ሲሆን ኦርቢቴል 901 የተሰኘው 2.1 ኪሎ ግራም የሚመዝን ነበር። ይህም በዚህ ዘመን ጥቅም ላይ ያሉእን 12 የአይፎን 14ኤስ ስልኮች ያህል ክብደት ነበረው።
የአጭር ጽሁፍ የመልዕክት ለውውጥ ከፍተኛው ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ዘመን በዓመት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የአጭር መልዕክቶች ልውውጥ ተደርጓል።
ከአስር ዓመት በፊትም የጽሁፍ መልዕክት ልውውጥን የሚያመለክተው "ቴክስቲንግ" የተሰኘው አዲስ ቃልም በ2010 (እአአ) ወደ መዝገበ ቃላት ተካተተ።
አጭር የጽሁፍ መልዕክት ለውውጥ አሁንም አገልገሎት እየሰጠ ቢሆንም፣ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ባሉ ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ እና ምስጢታዊነታቸው የተጠበቁ እንደ ዋትስአፕ ባሉ ዘዴዎች ተበልጧል።
የስታቲስታ መረጃ እንደሚጠቁመው እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 በዩናይትድ ኪንግደም 40 ቢሊዮን የጽሁፍ መልዕክቶች የተላኩ ሲሆን፣ በ2012 ከነበሩ 150 ቢሊዮን አሸቆልቁሏል።
በንጽጽር በአሁኑ ዘመን በዓለም ዙሪያ በዋትስአፕ አማካይነት በየቀኑ 100 ቢሊዮን መልዕክቶች ይላካሉ።
ይሁን እንጂ አጭር የጽሁፍ መልዕክት አሁንም ድረስ በተለያዩ ተቋማት አገለግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል። ከእነዚህም ውስጥ የህክምና ቀጠሮን ለመስታወስ እና ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ አገልግሎቶችን ለማግኘት የይለፍ ቁጥር ይልኩበታል።
ነገር ግን አጭር የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎት (SMS) ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የግንኙነት መስመር ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ ባለመሆኑ፣ ደኅንነቱ አስተማማኝ አይደለም። ቃ አይደረግለትም።
የአጭር የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎቱ ሲጀመር በአንድ ጊዜ መላክ የሚቻለው እስከ 160 ፊደላት፣ ቁጥሮችና ምልክቶች ያሉት መልዕክት ብቻ ነበር።
ይህ የመልዕክት ልውውጥ ሃሳብ ብቅ ያለው በአውሮፓውያኑ በ1980ዎቹ ሲሆን፣ የመጀመሪያው መልዕከት ወደ ሞባይል ስልክ ከመላኩ 10 ዓመት ቀደም ብሎ ነበር።
ቀደም ብለው የነበሩት ስልኮች ቁልፎቻቸው ወይም ኪቦርዳቻው ቁጥሮች ሲሆኑ በስራቸው ፊደላትን አያይዘዋል። ስለዚህ ለምሳሌ የእንግሊዝኛውን ‘ሲ’ ፊደል ለመጻፍ 1 ቁጥርን ሦስት ጊዜ መጫን የግድ ነበር።
የሞባይል ስልኮች በወቅቱ የተሰሩት የስልክ ጥሪ ለማድረግ እንዲሁም መልዕክቶችን ለመቀበል ብቻ ስለነበረ፤ የስልክ አምራቾቹ የእንግሊዝኛ ፊደላትን በተገቢው ሁኔታ አላካተቱም ነበር የሚሉት በሶልፎርድ ዩኒቨርሲቲ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ፕሮፌሰር የሆኑት ናይጀል ሊንጄ ናቸው።
በወቅቱ ለሰዎች የጽሁፍ መልዕክት እንዴት መቀበል እና መላክ እንደሚቻል ሥልጠና ይሰጥ እንደነበር ቤን ዉድ የተባሉት የቴክኖሎጂ ተንታኝ ያስታውሳሉ።
ጨምረውም ሰዎች የጽሁፍ መልዕክት የመላክና የመቀበልን ክህሎት በአጭር ጊዜ አዳብረው፣ በትናንሽ ስልኮች ላይ የፊደላቱን ቁልፍ ሳያያዩ በቀላሉ መልዕክት መላክ አስከመቻል ደርሰዋል።
በዚህ ዘመንም ሰዎች በስልኮቻቸው ከማውራት ይልቅ ወደ ስልኮቻቸው የሚላኩ መልዕክቶችን በመመልከት ሰፊ ጊዜን ይወስዳሉ።
ይህም የጽሁፍ መልዕክቶችን በስፋት እንደሚጠቀሙ አመላክች ነው ይላሉ ቤን ዉድ።