በሰባት የአፍሪካ አገራት 1,400 የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተመዘገበ

ታትሟል

እስከ ግንቦት ወር አጋማሽ ድረስ በሰባት የአፍሪካ አገራት ውስጥ በአጠቃላይ 1,400 የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ክስተት መመዝገቡን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

የበሽታው ክስተት የተመዘገበባቸው አገራት ካሜሩን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮንጎ ብራዛቪል እና ሴራሊዮን ሲሆኑ፣ ከአጠቃላይ ቁጥሩ 1,392ቱ በቫይረሱ የተጠረጠሩ እና 44ቱ ደግሞ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ነው።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በምዕራብና ማዕከላዊ አፍረካ አገራት ውስጥ ከዚህ በፊት ተከስቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ ቫይረሱ ቀደም ሲል ከተከሰተባቸው አገራት ውጪ ያልተስፋፋ ቢሆንም፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግን በሽታው የሚታይበት መልክዓ ምድራዊ አካባቢ እየሰፋ ይገኛል።

የጤና ድርጅቱ እንዳለው እስከ አውሮፓውያኑ 2019 ድረስ ቫይረሱ በናይጄሪያ በአብዛኛው በደቡባዊ ክፍሏ ውስጥ የነበረ ሲሆን፣ በተከታታይ ዓመታት ወደ ማዕከላዊ፣ ምሥራቃዊ እና ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ተስፋፍቷል።

በሽታው ከዚህ በፊት ታይቶባቸው በማይታወቁት አገራት ውስጥ መከሰቱ እንዲሁም ቫይረሱ ወደታየባቸው አገራት ያልተጓዙ ሰዎች ላይ በሽታው መገኘቱ አጠያያቂ ሆኗል።

ስለዚህም የዓለም ጤና ድርጅት አጠቃላዩን የቫይረሱን ሁኔታና በዓለም ዙሪያ የመከሰቱን ምክንያት ለማወቅ ከአጋሮቹ ጋር እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት “የተጠናከረ የበሽታ ቅኝት፣ በሽታው አሁን የደረሰበት ደረጃ በዝርዝር የመረዳት እንዲሁም የበለጠ የሚስፋፋም ከሆነ ለመቆጣጠር ዝግጁ በመሆን” አገራት የጋራ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።

ለበሽታው ምላሽ በመስጠት በኩል “አሁን በስፋት በሽታው ለተከሰተባቸው ምዕራባውያን አገራት እንዲሁም ለአፍሪካ የሚሆን ሁለት የተለያየ እርምጃ የመውሰድ ሁኔታ እንዳይከሰት ማድረግ አለብን” ሲሉ የአፍሪካ አካባቢ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ማጽሂዲሶ ማኤቲ ተናግረዋል።

የዝንጀሮ ፈንጣታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው እንደ አውሮፓውያኑ በ1970 በአፍሪካ ውስጥ ሲሆን፣ አብዛኛው የበሽታው ክስተት የተመዘገበው በገጠራማ እና ጥቅጥቅ ደን ባላባቸው አካባቢዎች ነበር።