ሊቨርፑል ከአርሰናል በ13 ነጥብ ርቆ ወደ ዋንጫ የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጥሎበታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሳምንቱ አጋማሽ የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ ድል የቀናው ሊቨርፑል ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 13 ማስፋት ችሏል።
ረቡዕ ምሽት በሜዳው አንፊልድ ኒውካስልን ያስተናገደው ሊቨርፑል ሁለት ለምንም ሲረታ ወደ ኖቲንግሀም ሜዳ ያቀናው አርሰናል ደግሞ ያለጎል ተለያይቷል።
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ ውድድሩ 10 ጨዋታዎች እየቀሩት በዚህ የነጥብ ልዩነት እየመራ ዋንጫውን ያጣ ክለብ የለም።
ቀያዮቹ በያዝነው የውድድር ዘመን አንድ ጊዜ ብቻ ነው ሽንፈት የቀመሱት።
የዋንጫ ተፎካካሪው አርሰናል ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘቱ ለሊቨርፑል ግስጋሴ አስተዋፅዖ አድርጓል።
የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ አርን ስሎት "አሁንም ገና ብዙ ይቀረናል። 10 ጨዋታዎች አሉ" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በበኩላቸው ከኖቲንግሀም ጨዋታ በፊት በሰጡት አስተያየት ዋንጫው ከአርሰናል እጅ ወጥቷል የሚለውን ሐሳብ "በፍፁም አልቀበለውም" ብለዋል።
ከጨዋታው በኋላ ደግሞ "አሁንም ከሳምንት ከሁለት ሳምንት በፊት ተመሳሳይ ነው። እኛ ማድረግ የምንችለው ጨዋታዎችን ማሸነፍ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የእግር ኳስ ተንታኞች ሊቨርፑል በያዝነው የውድድር ዘመን ኃያል ከመሆኑም ባለፈው የተቀናቃኞች መዳከም እንደረዳው ያስረዳሉ።
ረቡዕ ምሽት በሜዳቸው መድፈኞቹን ነጥብ ያስጣሉት ኖቲንግሀም ከአርሰናል በ6 ነጥብ ዝው ብለው ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የእግር ኳስ ትንተና እና ግምት የሚያወጣው ኦፕታ ሊቨርፑል ዋንጫውን የማንሳት ዕድሉ 98.7 በመቶ ሲሆን አርሰናል ደግሞ 1.3 በመቶ ነው ብሏል።
ሊቨርፑል 10 ጨዋታ እየቀረው በ13 ነጥብ ልዩነት ሊጉን ይመራል። አንድ ተጨማሪ ተስካካይ ጨዋታ ያለው አርሰናል ይከተላል።
ቀያዮቹ የ13 ነጥብ ልዩነታቸው አስጠብቀው ከቀጠሉ አራት ጨዋታዎች እየቀሯቸው በአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 26 ከቶተንሀም ጋር በሚኖራቸው ፍልሚያ የዋንጫው ባለቤት መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።
አርሰናል አንድ ቀሪ ጨዋታ አሸንፎ የነጥብ ልዩነቱ ወደ 10 ወርዶ በዚያው ከቀጠለ ደግሞ ሊቨርፑል ከቼልሲ ጋር በሚኖረው ጨዋታ የዋንጫ ባለድል መሆኑን ማወቅ ይችላል።
ይህ ከሆነ ሊቨርፑል ቀጥሎ ያለው ጨዋታ ከአርሰናል ሲሆን ፍልሚያው ደግሞ በአንፊልድ ይሆናል። በኦፕታ ስሌት መሠረት ሊቨርፑል የዋንጫ ባለቤት መሆኑን አረጋግጦ ከአርሰናል ጋር ሊጫወት ይችላል።
በሌሎች የሳምንቱ አጋማሽ ጨዋታዎች ማንቸስተር ሲቲ ቶተንሀምን 1-0 ሲረታ፤ አንድ ተጨዋች በቀይ የተሰናበተበት ዩናይትድ ኢፕስዊችን 3-2 አሸንፏል።












