የሰሜን ኮሪያ ተደጋጋሚ የኑክሌር ሙከራ የውሃ አካላት ላይ አደጋ ጋርጧል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
መቀመጫውን በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ያደረገ መንግሥታዊ ተቋም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰሜን ኮሪያውያን በውሃ ውስጥ በቀሩ የሬዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች መጋለጣቸውን አመላከተ።
ተቋሙ የኑክሌር ጨረሩ ንጥረ ነገር ከሰሜን ኮሪያ አልፎ በቻይና፣ በደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ላይም ስጋት እንደጋረጠ ነው የገለጸው።
በተጨማሪም በሰሜን ኮሪያ ፑንግሪ በተባለው አካባቢ ባለው ዋናው የኑክሌር ጣቢያ አቅራቢያ የነበሩ እና ወደ ደቡብ ኮርያ የሸሹ ለሬዲዮአክትቪ የነበራቸው ተጋላጭነት ላይ ምርመራ እንዲደረግ አሳስቧል።
በድምሩን ወደ 540 ሺህ የሚገመቱ ነዋሪዎች ለአደጋ መጋለጣቸውን ጠቁሟል።
ይህንን ያለው ተቋም እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ከደቡብ እና በሰሜን ኮሪያ፣ በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንፍም እና በካናዳ በመብት ተሟጋቾች እና በተመራማሪዎች በሴኦል የተመሠረተ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኒውክለር ባለሙያዎች የውሃ አካላት በኑክሌር ሊጎዱ እንደሚችሉ የተስማመቡት ሲሆን፣ መጠኑን ለመግመት ግን አዳጋች ነው ብለዋል።
የኑክሌር ጨረር የሰውነት ህዋሶችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ሊጎዱ እና ካንሰር ሊያስከትል ይችላል። በርካታ መርዛማ ነገሮችም ከራዲዮአክትቪ ጨረሮች ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚወሰን ነው።
ሰሜን ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ኑክሌር የሞከረችው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ሲሆን፣ እጅግ ኃያሎቹ ኑክሌር መሳሪያዎች ፑንግሪ በተባለው አካባቢ የተሞከሩ ናቸው።
ኮሪያን መልሶ ማዋሃድን የሚበረታታው እና በደቡብ ኮሪያ ያለው የውህደት ሚኒስቴር ለሬዲዮአክቲቭ ያለ ተጋላጭነት ላይ የሚደረግ ፍተሻ እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ነበር ያቋረጠው።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 እና 2018 አርባ ከሰሜን ኮሪያ የሸሹ ሰዎች ላይ በተደረገ የተጋላጭነት ምርመራ ዘጠኙ ሰዎች “አሳሳቢ” የዘረ መል መዛባት ማሳየታችን ሪፖርቶች ጠቁመዋል። የዘረመል መዛባት የተየባቸው ሰዎች ለሬዲዮአክቲቭ የተጋለጡ ናቸው።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ከሰሜን ኮሪያ የሸሹ ሰዎች የጤና ችግር ካጋጠማቸው እና የህክምና ድጋፍ ከጠየቁ የሚደረግላቸው ምርመራ ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁሟል።
የሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ መርሃ ግብር በፕሬዝዳንቷ ኪም ጆንግ ኡን ስር ተጠናክሮ ቀጥሏል። ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ዓመት በሰጡት አስተያየት ከዚህ በኃላ ጦርነት መከላከል ብቻ ሳይሆን ቀድሞ በማጥቃት ጦርነት ለማሸንፍ እንሰራለን ሲሉ ተደምጠዋል።












