በናይጄሪያ በጁምዓ ጸሎት ወቅት መስጅድ ተደርምሶ 7 ሰዎች ሞቱ

የተደረመሰው መስጅድ

የፎቶው ባለመብት, AMMAR RAJAB

ታትሟል

በናይጄሪያዋ ዛሪያ ከተማ በጁምዓ ጸሎት ወቅት ጥንታዊ መስጅድ ተደርምሶ የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ።

አደጋው ከትናንት በስቲያ አርብ ነሐሴ 5/2015 ዓ.ም. በደረሰበት ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች በመስጅዱ ውስጥ ጸሎት ላይ ነበሩ።

በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ በበርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል። አንድ የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል የተወሰዱት ሰዎች ቁጥር 20 ነው ሲል ዘግቧል።

ለመስጅዱ መደርመስ ምክንያት የሆነውን ለማወቅ ምርመራ ተጀምሯል።

አንድ የአካባቢው የሃማኖት መሪ ከመስጅዱ ግድግዳዎች በአንዱ ላይ የመሰንጠቅ ምልክት ሐሙስ ዕለት ታይቶ እንደነበረ ለአካባቢው መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

በጸሎት ወቅት የተደረመሰው መስጅድ ዕድሜው በመቶዎች የሚቆጠር ስለመሆኑ ተመላክቷል። ባለስልጣናት መስጅዱ የተገነባው በ1830ዎቹ ነው ይላሉ።

የዛሪያ ከተማ እስላማዊ ምክር ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት አብዱላሂ ክዋራባይ ቀድሞ የአራት ሰዎች አስክሬን መገኘቱን በመቀጠል ደግሞ የነብስ አድን ሠራተኞች ከፍርስራሽ ስር የተጨማሪ ሦስት ሰዎች አስክሬንን ማውጣታቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ አደጋው ከመድረሱ አንድ ቀን ከቀደም ብሎ በጥንታዊው መስጅድ ግድግዳ ላይ የታየውን መሰንጠቅ ለመጠገን የመሃንዲሶች ቡድን ተቋቁሞ ነበር ብለዋል።

አደጋው ያጋጠመባት ካዱና ግዛት አስተዳዳሪ ኡባ ሳኒ የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ በአስቸኳይ ምርመራ እንዲደረግ አዘው የተጎዱትን ለመርዳት ቃል ገብተዋል።

በናይጄሪያ በሕንጻዎች መደርመስ የሰዎች ሕይወት ማለፍ ዜና አዲስ ነገር አይደለም። ባለፈው ዓመት ብቻ በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ከ36 ያላነሱ ሕንጻዎች ተደርምሰው ነበር።