የኬንያ ፖሊስ ድጋሚ አደባባይ በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኮሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኬንያ ፖሊስ ድጋሜ አደባባይ በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኮሰ።
የአገሪቷ መከላከያ ሠራዊት አባላትን ጨምሮ በርካታ የፀጥታ ኃይሎች የተሰማሩ ሲሆን ተቃውሞው ከመጀመሩ አስቀድሞ በመዲናዋ በሚገኙ ወሳኝ ተቋማት አካባቢ የሚወስዱ መንገዶች ተዘግተዋል።
ይህ የሆነው ኬንያውያን የኑሮ ውድነትን ያባብሳል ያሉት የፋይናንስ ሕግ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ 22 ሰዎች መገደላቸው ከተዘገበ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።
በማግስቱ ረቡዕ ዕለትም ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ የተለያዩ ታክሶችን ለመጣል በታቀደው የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ ላይ ተግባራዊ እንዲሆን የሚፈቅደውን ፊርማቸውን እንደማያኖሩ አስታውቀዋል።
ሆኖም ተቃዋሚዎቹ በማክሰኞ ዕለቱ ተቃውሞ የተገደሉትን ለማሰብ በድጋሚ ለመሰባሰብ ቃል ገብተው ነበር።
የተወሰኑ ሌሎች ተቃዋሚዎች ደግሞ የፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት በሚገኝበት ቤተ መንግሥታቸው ለማምራት ዝተዋል።
ከተቃውሞው ጋር ግንኙነት ያላቸው ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦችም የባሰ እልቂት ያስከትላል በሚል እያስጠነቀቁ ነው።
ወደ ፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት የሚወስዱ መንገዶች የተዘጉ ሲሆን የጸጥታ ኃይሎችም ሞተረኞችንና እግረኞችን እየመለሱ ነው።
ቀደም ብሎ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በዋና ከተማዋ ለወትሮው እንቅስቃሴ የሚበዛባቸው የንግድ አካባቢዎች ጭር ማለታቸውን እና በርካታ የጸጥታ ኃይሎች በተሽከርካሪ ላይ ቅኝት ሲያደርጉ አሳይተዋል።
ከመዲናዋ ናይሮቢ ውጭ በሚገኙ ከተሞችም ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።
የኬንያ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው የባሕር ዳርቻዋ ከተማ ሞምባሳ የተሰባሰቡ ተቃዋሚዎች ሩቶ ከሥልጣን እንዲወርዱ በጩኸት ሲጠይቁ ነበር።በተቃዋሚዎቹ በሚወረወሩ ድንጋዮች እና ዘረፋዎች ምክንያትም የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል።
ማክሰኞ ዕለት ግጭት ያስተናገደችው የፕሬዚደንት ሩቶ የትውልድ ቦታ ኤልዶሬት ግን ዛሬ በአንጻሩ ተረጋግታለች።
ሆኖም በምዕራብ ኬንያ ሚጎሪ ግጭቶች ነበሩ።ሰልፈኞቹን ለመበተንም ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።
በኪሱሙም የተሰባሰቡ ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP












