ቲክቶክ በሕጻናት ግላዊ ደኅንነት ጥሰት ክስ ምክንያት ለአሜሪካ 400 ሚሊዮን ዶላር ሊከፍል ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ቲክቶክ የሕጻናትን ግላዊ ደኅንነት ጥበቃ ጥሷል በሚል በአሜሪካ የቀረበበት ክስ እንዲቋረጥ 400 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ።

ከዚህ ክስ ጋር በተያያዘ በቲክቶክ የተፈጸመ ከፍተኛው የክፍያ መጠን ነው።

ክሱ የቀረበው በአውሮፓውያኑ 2024 በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአስተዳደር ዘመን በነበረው የፍትሕ መስሪያ ቤት ነው።

ቲክቶክን የሚያስተዳድረው 'ባይትዳንስ' ዕድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች የሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናትን "ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ" ሰብስቧል በሚል ነበር የተከሰሰው።

መረጃ መሰብሰብ በአውሮፓውያኑ2000 ከወጣው የሕጻናት የበይነ መረብ የግላዊ መረጃ ጥበቃ ሕግ ጋር ይጣረሳል።

የአሜሪካ ግዛቶች ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታም ይሄንን ሕግ ጥሷል ብለው ከስሰዋል።

ተባባሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ብሬት ሽሜት "ይሄ ክስ ከተመሠረተበት ጊዜ አንጻር አሁን ላይ ልጆች እና ወላጆች የተሻለ ከለላ አላቸው" ብለዋል።

ጉግል የሚያስተዳድረው ዩትዩብ፤ የሕጻናት የበይነ መረብ የግላዊ መረጃ ጥበቃ ሕግን በመጣስ ተከስሶ 2019 ላይ 170 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል።

ቪድዮ ጌም አምራቹ ኤፒክ ጌምስ በተመሳሳይ ክስ 2022 ላይ 275 ሚሊዮን ዶላር ከፍሏል።

ሜታ በ29 የአሜሪካ ግዛቶች በቀረረበት ክስ በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ቅጣት ሊጣልበት ይችላል።

ሜታ የሚያስተዳድራቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የታዳጊዎችን ደኅንነት አልጠበቁም በሚል ከቀረቡት ክሶች አንዱ ባለፈው ሳምንት በፍርድ ቤት መታየት ጀምሯል።

ከሕዝብ በተውጣጡ ፍርድ ሰጪዎች (ጁሪ) የሚታየው ክስ ሜታ ከገጠሙት ፈተናዎች ትልቁ ነው።

ቲክቶክ አምና በአሜሪካ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ማቋረጡ ይታወሳል። ክሱ የቀረበበት ከዚህ በፊት ሲሆን፤ ክፍያ ለመፈጸም የተስማማው በቻይና ካሉ እንቅስቃሴዎቹ ጋር በተያያዘ ብቻ ነው።

ባይትዳንስ ያለው ሃብት 550 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ በቅርቡ የወጣ መረጃ ያሳያል።

በስምምነቱ መሠረት ባይትዳንስ እንዲሁም ቲክቶክ ለአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስትር 300 ሚሊዮን ዶላር በአፋጣኝ መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

በተጨማሪም የአገሪቱ የንግድ ኮሚሸን ጋር ባለው ስምምነት ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላሉ።

ከባይትዳንስ በፊት የነበረው 'ሚውዚካሊ' የተባለው ኩባንያም ከ13 ዓመት በታች ባሉ ታዳጊዎች የወላጅ ፈቃድ ባለመጠየቅ 5.7 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይጠበቅበት ነበር።

የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስትር ቲክቶክ ከሚፈጽመው ክፍያ በዘለለ ሌሎች እርምጃዎች ስለመወሰዳቸው አልገለጸም። ነገር ግን ክሱ ከተመሠረተ ወዲህ ቲክቶክ "ጉልህ መሻሻል" አሳይቷል ብሏል።

መሻሻል ታይቷል የተባለው በግል መረጃ ጥበቃ እና ታዳጊዎች ላይ በሚደረግ ቁጥጥር ነው።

ክሱ ሲመሠረት ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ከ170 ሚሊዮን በላይ ታዳጊዎች ቲክቶክ ይጠቀማሉ። ማኅበራዊ ሚዲያው "ሕጻናት ላይ ያነጣጠረ" እንደሆነም ተገልጿል።

ሕጻናት ያለ ወላጆቻቸው ፈቃድ ማኅበራዊ ሚዲያውን እንዲጠቀሙ በመፍቀዱም ቲክቶክ ተከስሷል።

ባይደን ቲክቶክ እንዲታገድ ወይም በአሜሪካ ያለው ድርሻ እንዲሸጥ ወይም እንዲከስም ጫና ሲያሳድሩ ነበር።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቲክቶክ የአሜሪካ ድርሻ እንዲሸጥ የወሰኑት አምና ነው።

ቲክቶክ አስተያየት እንዲሰጥ ከቢቢሲ ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም።