ዶናልድ ትራምፕ በተከፈተባቸው ምርመራ ዙሪያ ቃላቸውን ለመስጠት አሻፈረኝ አሉ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኒውዮርክ በቤተሰብ ንግድ ዙሪያ መንግሥት እያደረገ ለሚገኘው ምርመራ ቃላቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

 ትራምፕ ትናንት በኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ከተከፈተባቸው ምርመራ ጋር በተያያዘ ቃል ለመስጠት የተገኙ ቢሆንም ጠቅላይ አቃቤ ህግን በመኮነን ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።  

የትራምፕ የንግድ ድርጀት ብድር እና የግብር እፎይታን ለማግኘት የተሳሳተ የሃብት መጠን አሳውቋል የሚል ክስ በመንግሰት ቀርቦበታል

ሆኖም ትራምፕ ይህንን ክስ አይቀበሉትም።

ትራምፕ ቃለ መሃላ ፈጽመው የእምንት ክህደት ቃላቸው የሚሰጡበት ስፍራ ላይ የተገኙ ሲሆን በንባብ ባሰሙት መግለጫ የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህጓን ተችተዋል።

እዚህ ለመድረስ ብዙ ዓመታት እና ሚሊዮን ዶላሮች ወጥቷል ያሉ ሲሆን "በአሜሪካ ህገ መንግሥት በተጠቀሰው መብት መሰረት ቃሌን ላለመስጠት ወስኛለሁ" ብለዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትናንት ረቡዕ በተካሄደው ቃል የመስጠት ሂደት ላይ ትራምፕ ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር ብሏል። ሆኖም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቃላቸውን ሳይሰጡ መቅረታቸውን አረጋግጧል።

“የትኛውም የአመራር ደረጃ ጠቅላይ አቃቤ ህጓ ህግ እና እውነታን መሰረት አድርገው ይቀጥላሉ ” ያለው መግለጫው ምርመራው እንደሚቀጥል ገልጿል።

ይህ የትራምፕ ድርጊት የተሰማው በፍሎሪዳ የሚገኘው ቤታቸው ኤፍ ቢ አይ ፍተሻ ካደረገ ከቀናት በሃላ ነው።

የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምርመራ እያደረገ በሚገኝበት የፍትሃብሄር ወንጀል ሲሆን በማንታን አውራጃ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ደግሞ በወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የህግ አዋቂዎች ትራምፕ ቃላቸውን ከመስጠት አሻፈረኝ ያሉበት ምክንያት ምን አልባት ምላሻቸው በምርመራ ወቅት የራሳቸው ቃል ለምርመራው አጋዥ እንዳይሆን ሰግተው ነው የሚል ግምታቸውን ሰጥተዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳናት ራሳቸው እንዲከላከሉ ጥሪ የቀረበላቸው ሰዎች ክስ በሚመሰረትባቸው ጊዜ ራሳቸውን እንዲከላከሉ በሚያዘው የህግ አግባብ መሰረት ሲሆን ተከሳሾች ቃላቸውን ያለመሰጠት መብታቸው ግን የተጠበቀ ነው።

የቃል መስጠቱ ሂደቱ ረጅም እረፍትን ጨምሮ አራት ሰዓት እንደፈጀ ጠበቃቸው ተናገረዋል።

እየተቀረጸ በነበረው የቃል መስጠት ሂደቱ ላይ ትራምፕ ቃል ያለመስጠት መብታቸውን በተመለከተ ንባብ አሰምተዋል።  በተጨማሪም በንባባቸው ጠቅላይ አቃቤ ህጓን ኮንነዋል።

ለሚጠየቁት ሁሉም ጥያቄዎች ተመሳሳይ ምላሽ ሲሰጡም ነበር ተብሏል።