ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኤለን ሾው የሚታወቀው ዲጄ ‘ትዊች’ በ40 ዓመቱ ሕይወቱ አለፈ
‘ትዊች’ በሚለው ስሙ የሚታወቀው አሜሪካዊው ዲጄ፣ ዳንሰኛ፣ ተዋናይና ፕሮዲውሰር ስቴፈን ቦስ እራሱን ማጥፋቱ ተገለጸ።
የ40 ዓመቱ ትዊች በኤለን ዲጀነረስ በሚዘጋጀው ኤለን ሾው ላይ በዲጄነትና በመደነስ በስፋት ይታወቃል።
ባለቤቱ አሊሰን ሆልከር ቦስ “የቤታችን ካስማ ነበር። ተወዳጅ አባትና ባል ነበር። በአድናቂዎቹም ይወደዳል” ስትል ለፒፕል መጽሔት ተናግራለች።
ኤለን “ዜናውን ስሰማ ልቤ ተሰበረ። በፍቅርና ብርሃን የተሞላ ነበር። በሙሉ ልቤ የምወደው ቤተሰቤ ነበር። እጅግ ይናፍቀኛል” ስትል ትዊት አድርጋለች።
‘ብሌድስ ኦፍ ግሎሪ’ እና ‘ሄርስፕሬይ’ በተባሉ ፊልሞች ሲተውን ነበር ዕውቅና ያገኘው። እአአ በ2008 ‘ሶ ዩ ቲንክ ዩ ካን ዳንስ’ የተባለው የዳንስ ውድድር ላይ የመጨረሻው ዙር ደርሷል። ኋላ ላይ የውድድሩ ዳኛ ሆኗል።
በኤሚ የምርጥ ዳንስ ቅንብር ዘርፍ ከትዊች ዳንሶች አንዱ ታጭቶ ነበር።
‘ስቴፕ አፕ’ እና ‘ማጂክ ማይክ’ በተባሉት ፊልሞችም የሚታወቅ ሲሆን በ2020 የኤለን ሾው ዋና ፕሮዲውሰር ሆኗል።
ኤለን ሾው ከመጠናቀቁ በፊት ነበር የዋና ፕሮዲውሰርነት ቦታ የተሰጠው።
በዕለቱ ኤለን ትዊችን “ከአሥር ዓመት በፊት ሕይወቴን የቀየረ ሰው ተዋወቅኩ። እሱም ትዊች ነው። በጣም ነው የምወድህ። ሁሌም በዳንስ ወይም በዘፈን ታስቀኛለህ” ብላው ነበር።
ዳንሰኛ ባለቤቱ “ስቴፈን የትኛውንም ክፍል ያደምቃል። ለቤተሰቡ፣ ለጓደኞቹና ለማኅበረሰቡ ዋጋ ይሰጣል። በፍቅርና በብርሃን መንገድ የሚቀድ ሰው ነበር። ስቴፈን፣ እንወድሀለን፣ እንናፍቅሀለን” ስትል ገልጻዋለች።
በዳንስ ውድድር ላይ የተገናኙት ጥንዶቹ ሦስት ልጆች አፍርተዋል። በኤለን ሾውም በጋራ ይቀርቡ ነበር።
በተለያየ የመዝናኛ ዘርፍ ያሉ ታዋቂ ግለሰቦች ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።