ትራምፕ የግማሽ ዘመን ምርጫ በተቃረበባት አሜሪካ ያለው የምርጫ ሥርዓት ለጣልቃ ገብነት "እጅጉን የተጋለጠ ነው" አሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቻይና በ2020 ምርጫ ጣልቃ እንደገባች እንዲሁም በአሜሪካ የድምፅ መስጫ ሥርዓቶች ውስጥ "አስደንጋጭ ተጋላጭነቶች" መኖራቸውን ተናገሩ።

ሐሙስ ዕለት በዋይት ሐውስ መግለጫ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚህ ቀደምም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በተሸነፉበት የ2020 ምርጫ ላይ የምርጫ ማጭበርበር እንዲሁም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደተፈጸመ ሲናገሩ ቆይተዋል።

ፕሬዝዳንቱ የሚያነሷቸው እነዚህ ክሶች ተጨባጭ ማስረጃ ያልቀረበባቸው ናቸው።

ትራምፕ የአሜሪካ የግማሽ ሥልጣን ዘመን ምርጫ ሊካሄድ ሦስት ወራት ሲቀሩት ያሰሙት ይህ ንግግር ለአንድ ሰዓት የዘለቀ ነው።

በመግለጫቸው ቻይና በ2020 ምርጫ ባይደን እንዲያሸንፉ ሠርታለች የሚለውን ክሳቸውን ለመደገፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥጥራዊ የስለላ ሰነዶችን ይፋ አድርገዋል።

የአሜሪካ የስለላ ማኅበረሰብ ከዚህ ቀደም ቻይና ጣልቃ አልገባችም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር።

ትራምፕ ከበርካታ ከፍተኛ ኃላፊዎቻቸው ፊት ለፊት ሆነው በሰጡት መግለጫ ላይ ጋዜጠኞች ጥያቄ ማቅረብ አልቻሉም።

ፕሬዝዳንቱ ቻይና ግላዊ መረጃዎችን ጨምሮ የ220 ሚሊዮን መራጮችን ሰነዶች "በሕገ-ወጥ መንገድ አግኝታለች" ሲሉ ከስሰዋል።

በ18 ግዛቶች ውስጥ የሚገኝ የመራጮች መረጃ "በቻይና ተገዝቷል፣ ተሰርቋል ወይም ተመንትፏል (ሀክ)" ያሉት ትራምፕ፤ "ማስጠንቀቂያውን የማሰማት ኃላፊነት የነበረባቸው" አካላት ግን ስለጉዳዩ የደረሱበትን ለመንግሥት ባለሥልጣናት ወይም ለኮንግረሱ ይፋ አላደረጉም ሲሉ ከስሰዋል።

በተጨማሪም አሜሪካ የድምጽ መስጫ ማሽኖች እንደ ሩሲያ፣ ቻይና እና ኢራን ላሉ የውጭ ጠላቶች ጣልቃ ገብነት "በከፍተኛ መጠን የተጋለጡ" መሆናቸውን ተናግረዋል።

ትራምፕ፤ ቻይና የምርጫ ሥርዓቶችን ለመቀየር ወይም በምርጫው ውጤት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር በሕገ ወጥ መንገድ የሰበሰበችውን መረጃ ተጠቅማለች ለሚለው ንግግራቸው ማስረጃ አላቀረቡም።

በዋሽግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ስለዚህ ክስ ለዜና ወኪሉ ሮይተርስ በሰጠው ምላሽ፤ ቤጂንግ "በፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች ውስጥ በጭራሽ ጣልቃ አልገባችም፤ ወደፊትም አትገባም" ብሏል።

ቢቢሲ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።

ዴሞክራቶች በበኩላቸው ትራምፕ በመጪው ኅዳር የሚካሄደው እና በቀረው የሥልጣን ዘመናቸው የኮንግረስ ቁጥጥር ማን እጅ ላይ ይወድቃል የሚለውን የሚወስነው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ላይ ጥርጣሬ ለመዝራት እየሞከሩ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

ሴኔት ውስጥ ታዋቂ ዴሞክራት የሆኑት ቸክ ሹመር ከትራምፕ ንግግር በኋላ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ፤ "ግልጽ እንሁን፤ በአሜሪካ መራጮች መሪዎቻቸውን ይመርጣሉ እንጂ መሪዎች መራጮችን አይመርጡም" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያቀረቡት ክስ የአሜሪካ ስለላ ተቋማት ባደረጉት ግምገማ ከደረሱበት ድምዳሜ ይቃረናል።

አሜሪካ ብሔራዊ የስለላ ምክር ቤት 2021 ላይ ባወጣው ሪፖርት፤ ቻይና በ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ እንዳልገባች "ከፍተኛ መተማመን" እንዳለው አስታውቋል።

ትራምፕ የዋይት ሐውስ ንግግራቸውን ያደረጉት፤ ያላቸው ተቀባይነት በ37 በመቶ መውረዱን የሚያሳይ የሕዝብ አስተያየት ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው።

'ዋሽንግተን ፖስት-ኢፕሶስ' በተባለው ተቋም የተሰበሰበው አስተያየት በርካታ መራጮች በኑሮ ውድነት እና ከኢራን ጋር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ስለ ትራምፕ ያላቸው ምልከታ ጨለምተኛ መሆኑን አመላክቷል።