በሱዳን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት እየተራቡ ነው- ተመድ

የሱዳን ህጻናት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በእርስ በርስ ጦርነት እየተናወጠች ያለችው ሱዳን በአለም ላይ ለህጻናት አስከፊ ከሆኑ ቦታዎች አንዷ መሆኗን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ኃላፊ (ዩኒሴፍ) ገለጹ።

በአገሪቷ በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህጻናት የተፈናቀሉ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትም የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ኃላፊዋ ካትሪን ራስል ተናግረዋል።

በአገሪቱ የገጠመው ረሃብም የከፋ እንዳይሆን በርካታ የረድዔት ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።

የሱዳን የምግብ ስርዓት መበጣጠሱን የተናገሩት ኃላፊዋ ሁለቱ ተፋላሚ አካላት የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል የእርዳታ አቅርቦቶችን እየገደቡ ነው ሲሉ ከሰዋቸዋል።

በአገሪቱ በተከሰተው የረሃብ ቀውስ ዋነኛ ተጠቂ እየሆኑ ያሉት ህጻናት መሆናቸውን ለቢቢሲ የገለጹት ካትሪን ራስል ዘጠኝ ሚሊዮን የሚሆኑት በመደበኛነት በቂ ምግብ አያገኙም እንዲሁም ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ በከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው ብለዋል።

“እርምጃ የምንወስድበት ጊዜ እያለፈ ነው። አሁንም ይህንን ለመግታት እርምጃዎችን ካልወሰድን የበለጠ እየከፋ ይሄዳል” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም “በከፋ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ እና በረሃብ ቸነፈር ላይ ላሉ ህጻናት ጊዜው ሳይረፍድ አሁን መደረስ እንዳለበት” አሳስበዋል።

ቢቢሲ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ያናገራቸው የምግብ ዋስትና ባለሙያ እስከ መጪው መስከረም ድረስ 70 በመቶው የሱዳን ህዝብ በከፋ ረሃብ ውስጥ እንደሚገባ ገልጸው ነበር።

“ይህም ሁኔታ ወደ ሁለት ሚሊዮን ተኩል ወይም ከዚያ በላይ ሞቶችን ሊያስከትል ይችላል። ከፍተኛ የምግብ እጥረት ስላለ እስከ አራት ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል” ሲሉ ቲሞ ጋዝቤክ ተናግረዋል።

ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እየተፋለሙ ያሉት የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አገሪቱን ለሰብዓዊ ቀውስ እና እልቂት እየዳረጓት ይገኛሉ።

ጦሩ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሚቆጣጠራቸው ስፍራዎች ላይ ምግብ እና ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ አድርጓል።

የፈጥኖ ደራሹ ኃይል በከፍተኛ ምዝበራ ላይ በመሳተፍ እየተወቀሰ ሲሆን ሁለት ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሉባትን ኤል ፋሽርን ከአንድ ወር በላይ በከበባ ውስጥ አስገብቷታል።

ኃላፊዋ እነዚህ አካላት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀሙ ነው በሚለው ላይ ምንም መናገር እንደማይችሉ ቢገልጹም የተፈጠረው የረሃብ ቀውስ “መቶ በመቶ ሰው ሰራሽ ነው” ብለዋል።

“ለእኛ ተግዳሮት የሆነው የምግብ ወይም የእርዳታ እጥረት አይደለም። ነገር ግን ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ማድረስ አልቻልንም ይህ ነው ቀውሱ” ብለዋል።

አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት የተፈናቀሉባት ሱዳን ከአለም ከፍተኛውን አኃዝ የያዘች ሲሆን ለወደፊቱም የአገሪቱን እጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ይከተዋል ተብሏል።