ለዓለም ዋንጫ ወደ ኳታር በእግሩ እየተጓዘ የነበረው ስፔናዊ ኢራን ውስጥ ታሰረ
![ነሐሴ ወር ላይ ሳንቲያጎ ሳንቸዝ [በቀኝ በኩል] እና ጓደኛው በኢራቅ ኩርዲስታን ግዛት አብረው ሲጓዙ](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/0e10/live/445e6c90-5698-11ed-ac87-630245663c6a.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኳታር በሚካሄደው የ2022 የዓለም ዋንጫ ለመታደም ከስፔን ማድሪድ ተነስቶ ወደ ኳታር በእግር እየተጓዘ የነበረው ስፔናዊ ኢራን ውስጥ መታሰሩ ተሰማ።
የ41 ዓመቱ የእግር ተጓዥ እና የእግር ኳስ ደጋፊ ሳንዲያጎ ሳንቼዝ ጉዞውን የጀመረው ጥር ወር ላይ ሲሆን ለእስር የተዳረገው ኳታር ከመድረሱ የመጨረሻዋ አገር በሆነችው ኢራን ነው።
ሳንቼዝ ጉዞውን በተመለከተም በኢንስታግራም ገጹ ላይ በተከታታይ ፎቶዎችን ሲያጋራ ቆይቷል።
ለመጨረሻ ጊዜም የኢራን መዳረሻ ወደ ሆነው ሰሜናዊ ኢራቅ የመጨረሻ መንደር መድረሱን ገልጾ ከፎቶ ጋር በኢንስታግራም ገጹ ላይ አጋርቷል።
ከዚያ በኋላ ግን ምንም ዓይነት ፎቶግራፎችን በገጹ ላይ ያለጠፈ ሲሆን ከእርሱ ጋር የነበረው ግንኙነት ከ26 ቀናት በፊት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።
ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ በሳንቼዝ መጥፋት ለሳምንታት ሲጨነቁ ከቆዩ በኋላ ግለሰቡ በኢራን መዲና ቴህራን እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ተሰምቷል።
ከጓደኞቹ መካከል አንዱ የሆነው ፍራንቾ ሳላማንካ፣ ሳንቲያጎ መታሰሩን እና አሁን ላይ በቴህራን እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ስለ ጉዳዩ በቢቢሲ የተጠየቀው የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በቴህራን የሚገኘው ኤምባሲያቸው ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር መነጋገሩን ገልጾ፣ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ግን ተቆጥቧል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም።
ሳንቼዝ ወደ ኢራን ከገባ በኋላ ምን እንደገጠመው እስካሁን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።
በኢራቅ እና በኩርዲስታን ድንበር ላይ ተቀማጭነቱን ያደረገው ሄንጋው የሰብዓዊ መብት ድርጅት ስማቸውን ያልገለጸቸው ምንጮቹን ጠቅሶ፣ ሳንቼዝ፣ “ሂጃብሽን በአግባቡ አለበሽም” በሚል ታስራ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለች የሞተችውን የማሻ አሚኒን የመቃብር ሥፍራ ከጎበኘ በኋላ በኢራን የጸጥታ ኃይሎች መወሰዱን ገልጿል።
የ22 ዓመቷ አሚኒ ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ መሞቷን ተከትሎ በመላ አገሪቷ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
ተቀማጭነቱን በኖርዌይ ያደረገው የኢራን ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን፣ ተቃውሞውን ተከትሎ 29 ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 234 ተቃዋሚዎች በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ገልጿል። የኢራን መሪዎች በበኩላቸው የተፈጠረው አለመረጋጋት "በጠላት የውጭ ኃይሎች" የተቀሰቀሰ ነው ብለውታል።
ሳላማንካ፣ ሳንቼዝ ከመታሰሩ በፊት በስልክ አውርተዋል። በኢራን በሚያደርገው ጉዞም ከእርሱ ጋር ለመቀላቀል አብሮት ለመሄድ እቅድ ነበረው።ነገር ግን በሥራ ምክንያት ሳይሳካለት ቀርቶ ሳላማንካ እዚያው ስፔን ቀረ።
ሳላማንካ እንደሚለው ጓደኛው ሳንቼዝ በአውሮፓውያኑ 2019 ወደ ሳዑዲ አረቢያ ባደረገው ጉዞ በጎበኛት ኢራን በኩል የመሄድ እድል በማግኘቱ ደስተኛ ነበር።
“የኢራን ሕዝቦች በሚገባ ተንከባክበውታል። በጣም ጥሩ ሕዝቦች ናቸው። ብዙም ረድተውታል” ብሏል ሳላማንካ።
የቀድሞው የአየር ኃይል አባል የነበረውና የሪል ማድሪድ ደጋፊ የሆነው ሳንቼዝ ፣ ወደ ወደ ቴህራን ለመሄድ አቅዶ ነበር። እዚያም አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቃለ መጠይቅ ሊያደርግለት ፈልጎ ነበር።
ከዚያም በጀልባ ወደ ኳታር ወደሚያመራበትና በደቡብ ኢራን በሚገኘው ባንዳር አባስ ወደብ ለማምራት እቅድ ነበረው።
ሳንቼዝ በኢራን ኢንተርኔት የማግኘት እድሉ አነስተኛ እንደሆነ ለቤተሰቦቹ እና ለጓደኞቹ ተናግሮ ስለነበር መጀመሪያ ላይ ድምጹ ሲጠፋባቸው በኢንተርኔት ችግር ምክንያት ሊሆን ይችላል በሚል ብዙም አልተጨነቁም ነበር።
ሆኖም ለአስር ተከታታይ ቀናት ቤተሰቦቹ ጋር ባለመገናኘቱ ስጋታቸው እያየለ መጥቶ ቤተሰቦቹ ልጃቸው መጥፋቱን አሳውቀዋል።
“በጣም ተጨንቀናል። እኔ እና ባለቤቴ ለቅሷችንን ማቆም አልቻልንም" ሲሉ እናቱ ሴሊያ ኮገዶር ለአሶሼትድ ፕረስ የዜና ወኪል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ተናግረዋል።
ሳንቼዝ እስር ቤት እንደሆነ በስፔን መንግሥት የተነገራቸው ሲሆን የእስሩ ምክንያት ምን እንደሆነ ግን በይፋ አልተገለጸም።
ሳንቼዝ ኢራቅ ከመግባቱ በፊት በአውሮፓ እና በቱርክ እያቆራረጠ በድንኳን፣ በሆቴል እና በሰዎች ቤት ውስጥ እያደረ ነበር ጉዞውን ያደረገው።












