ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተመኘው ዩኒቨርስቲ ለመግባት 4 ሺህ ኪሎ ሜትር በሳይክል የተጓዘውን ወጣት ዊል ስሚዝ ሸለመው
ይመኘው የነበረ ዩኒቨርስቲ ለመግባት 4,000 ኪሎ ሜትር በሳይክል የተጓዘው ወጣት ከታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ ዊል ስሚዝ ሽልማት አግኝቷል።
ማማዱ ሳፋያው ባሪ የተባለው የጋያና ወጣት ግብፅ የሚገኝ ዩኒቨርስቲ ለመግባት 4 ሺህ ኪሎ ሜትር በሳይክል መጓዙን ቢቢሲ ያለፈው መስከረም መዘገቡ ይታወሳል።
ወጣቱ በምዕራብ አፍሪካ ለአራት ወራት ተጉዟል። ነጻ የትምህርት ዕድል ያገኘበት በግብፅ መዲና ካይሮ የሚገኘው አል-አዝሐር ዩኒቨርስቲም ደርሷል።
የቢቢሲን ዘገባ የተመለከተው ዊል ስሚዝ ለማማዱ ላፕቶፕና ሳይክል ሸልሟል።
ባለ ትዳር እና የአንድ ልጅ አባት የሆነው ተማሪ በተመኘው ዩኒቨርሲቲ የፈቀደውን ትምህርት ለመከታተል ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቶጎ፣ ቤኒን፣ ኒጀር እና ቻድ በሳይክል አቆራርጧል።
በተዋናዩ የዩቲዮብ ገጽ ላይ የተላለፈ ቪድዮ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት “ባለቤትህና ልጅህ ጋያና እንዳሉ አውቃለሁ። ስለዚህ እየተመላለስክ የምትጠይቅበት ወይም እነሱን ወደ ግብፅ የምትወስድበት የአውሮፕላን ትኬት እሰጥሀለሁ” ብሏል።
ዊል ስሚዝ በማማዱ ታሪክ “ልቡ እንደተነካና በጣም እንዳነቃቃው” ተናግሯል።
ስጦታዎቹን ለምን እንደሰጠው ሲገልጽም “የቀጣይ ሕይወትህ አካል መሆን ስለምፈልግ ነው” ብሎታል።
ተዋናዩ ጨምሮም “በጉዞህ ላግዝህ እፈልጋለሁ” ብሏል።
ከዊል ስሚዝ በድንገት በቪድዮ ሲደወልለትና ስጦታዎቹ ሲሰጡት የተደሰተው ማማዱ “ወላሂ እንዴት እንደማመሰግንህ አላውቅም። በቃ እንዴት እንደማመሰግንህ አላውቅም” ብሎታል ለተዋናዩ።
ዊል ስሚዝ በበኩሉ የማማዱ ቆራጥነት “አንድ ሰው ከወሰነና ያመነበትን ነገር ለማድረግ ቆርጦ ከተነሳ ዓለም ልትረዳው እንደምትፈቅድ ማሳያ ነው” ብሏል።
የ25 ዓመቱ ወጣት ከቢቢሲ ጋር አድርጎ በነበረው ቆይታ፣ ግብፅ ለመድረስ ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች የሚቆጣጠሯቸውን አካባቢዎች ማለፍ እና መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸውን የአፍሪካ አገራት ድንበር መሻገር እንደነበረበት ገልጿል።
ማማዱ ከብዙ ጥረት በኋላ የግብፁ ጥንታዊ አል-አዝሐር ዩኒቨርሲቲ ነጻ የትምህርት ዕድል በማግኘቱ “በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
በግብፁ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለመከታተል ክፍያ መፈጸም ስለማይችልና ወደ ግብፅ ለመጓዝም የአየር ቲኬት ለመቁረጥ ገንዘብ ስለሌለው በሳይክል አደገኛውን ጉዞ ለማድረግ መወሰኑን ገልጾ ነበር።