በህንድ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ቢያንስ 50 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሰሜናዊ ህንድ ሂማቻል ፕራዴሽ ግዛት ሰሞኑን ከፍተኛ ዝናብ ዘንቧል።
ይህ ከባድ ዝናብ የፈጠረው ጎርፍ እና ተያያዥ ምክንያቶች በግዛቷ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ቢያንስ 50 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
በግዛቷ መዲና በሆነችው ሺምላ ብቻ አንድ ቤተ ዕምነት ተደርምሶ 9 ሰዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፏል ተብሏል።
ባለስልጣናት እንደሚሉት በፍርስራሹ ውስጥ በርካታ ሰዎች ተደብቀው ሊሆን ይችላል።
በተራራማነቷ በምትታወቀው ግዛት የጣለው ከባድ ዝናብ ደራሽ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ማጋጠሙን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የግዛቷ መንገዶች የተዘጋጉ ሲሆን አንድ የባቡር ሃዲድም በተፈጠረው ጎርፍ የተወሰነ ክፍሉ ተጠርጎ ተወስዷል ተብሏል።
የአካባቢው ባለስልጣናት ሁኔታው አስደንጋጭ መሆኑን በመግለጽ ይህንንም የሚያመለክቱ ፎቶ እና ቪዲዮዎችን በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጋርተዋል።
በቪዲዮው ላይ እንደሚታየው ከባድ ጎርፍ መንገዶችን እየቆረጠ እና ቤቶችን እየደረማመሰ ሲያጥለቀልቅ ተስተውሏል። በዚህ አደገኛ ጎርፍ ሰዎች መወሰዳቸውንም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።
የሂማቻል ፕራዴሽ ግዛት በተለይም ደግሞ ዋና ከተማዋ ሺምላ በርካታ ጎብኝዎችን በየዓመቱ የምታስተናግድ ውብ ተፈጥሮ ያላት ግዛት ነች።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግዛቷ በከፍተኛ ዝናብ እና ይህንንም ተከትሎ በሚፈጠር ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የቱሪዝም ሃብቷን እያሟጠጠው ነው።
ለክስተቱ ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ቢችሉም በዋናነት ግን የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚወስድ ሙያተኞች ያብራራሉ።
የኢንዱስትሪ ዘመን ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ዓለም በ1.1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሙቀት መጠኗ ጨምሯል። አሁንም የሙቀት መጠን መጨመሩ የቀጠለ ሲሆን መንግሥታት የተለየ ርምጃ ካልወሰዱ ችግሩ በፍጥነት ይባባሳል።
ሂማቻል ፕራዴሽ ግዛት በርካታ የህንድ ቤተ እምነቶች የሚገኙባት ግዛት ስትሆን በዚህም ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ወደ ስፍራው ያመራሉ። ነገር ግን ሰሞኑን የዘነበው ከባድ ዝናብ ብዙዎቹን ጉዳት አድርሶባቸዋል።
በሂንዱ ዕምነት ከሚታወቁት አራቱ ቅዱስ ቦታቸች መካከል አንዱ የሆነው ቻር ዳም ያጥራ ሰኞ ዕለት በዝናቡ ምክንያት ለሁለት ቀናት እንዲዘጋ ተደርጓል።
በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚዘዋወሩ ምስሎች እንደሚያሳዩት የቤተ እምነቱ የተወሰነ ክፍል በጎርፉ ጥቃት ደርሶበታል።












