ፊሊፒንስን በመታው ከባድ አውሎ ንፋስ አራት የነፍስ አድን ሠራተኞች ሞቱ

በጎርፍ በተጥለቀለቀ መንገድ ላይ የሚታዩ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ፊሊፒንስን የመታውን አውሎ ንፋስ ተከትሎ በተከሰተ ጎርፍ ምክንያት አራት የነፍስ አድን ሠራተኞች ሕይወታቸውን አጡ።

ከከባድ አውሎ ነፋሱ በኋላ ጎርፍ የተከሰተ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸዋል።

ከርዕሰ መዲናዋ ማኒላ በስተሰሜን በሚገኘው ሳን ሚጌል አውራጃ በሥራ ላይ የነበሩ የነፍስ አድን ሠራተኞች ናቸው በድንገተኛ ጎርፍ የተወሰዱት።

አውራጃው በጎርፉ ክፉኛ ከተጠቁት መካከል አንዱ ሲሆን አንዳንድ ነዋሪዎች ቤታቸው ጣሪያ ላይ ለመሆን ተገደዋል።

ኑሩ ተብሎ ስያሜ የተሰጠው አውሎ ንፋስ በሰዓት 240 ኪሎ ሜትር ይፈጥን ነበር ተብሏል። 110 ሚሊዮን ከሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ግማሹ በሚኖርባትን ሉዞን ማጥቃቱም ታውቋል።

በአካባቢው ነዋሪዎች ካርዲንግ በመባል የሚታወቀው አውሎ ነፋስ መጀመሪያ ላይ ከባድ ነበረ ቢሆንም እሑድ ዕለት መቀዛቀዙ ተነግሯል።  ሰኞ አመሻሽ ላይ ከፊሊፒንስ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በሳን ሚጌል አውራጃ ሳን ቪንሴንቴ በተባለች መንደር አንድ ሰው ውሃውን ከበሩ ለማራቅ ሲሞክር ታይቷል።

ሌላዋ በቤቷ ጣራ ላይ ቆማ የአገሪቱ መሪዎች "በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ማተኮር አለባቸው" ስትል ጮክ ብላ ስትናገር ተደምጣለች።

በመንደሩ የጎርፍ አደጋ ከጠዋቱ የደረሰ ሲሆን ውሃው እየቀነሰ መምጣቱ ተነግሯል።

ከ74,000 በላይ ሰዎች ከአውሎ ነፋሱ አካባቢ እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን ባለሥልጣናቱ ቀደም ብለው በዋና ከተማዋ ማኒላ "ከባድ የጎርፍ አደጋ" ሊደርስ ይችላል ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ጉዳት ወይም የሕይወት መጥፋት ስለመኖሩ የተገለጸ ነገር የለም።

የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር "ቢያንስ በዚህ ጊዜ ዕድለኞች ልንሆን እንችላለን ብዬ አስባለሁ። ባለፉት ሁለት ቀናት ካደረግናቸው ነገሮች መረዳት የሚቻለው ዝግጅት በጣም በጣም አስፈላጊ መሆኑን ነው" ሲሉም አክለዋል።

በጎርፍ በተጥለቀለቀ መንገድ ላይ የሚታዩ ሰዎች

"እስካሁን ችግሩ አላበቃም። በሁለት እግር ቆመናል የምንለው አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ይመስለኛል" ብለዋል።

ማርኮስ ግብዓቶች በአውሮፕላን እንዲላኩ እና ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው የጽዳት መሣሪያዎች እንዲሰጡ አዘዋል።

ከማኒላ በስተምሥራቅ በምትገኘው ክዌዘን ግዛት ዓሳ አስጋሪዎች ወደ ባሕር እንዳያመሩ ተከልክለው የነበረ ሲሆን አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ መብራት ተቋርጦባቸዋል ተብሏል።

በተከሰተው አደጋ ምክንያት በረራዎች እና የጀልባ አገልግሎቶች ተሰርዘዋል። ፕሬዘዳንት ማርኮስ በሉዞን የሚገኙ ሁሉንም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ትምህር እንዲዘጉ አዘዋል።