በኡጋንዳ ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ያለው ታጣቂ ቡድን ሕጻናትን ጨምሮ 40 ሰዎችን ገደለ

ጥቃት የተፈጸመበት ት/ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በምዕራብ ኡጋንዳ ከጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን ኢስላሚክ ስቴት ጋር ግንኙነት አለው የተባለ ታጣቂ ቡድን ሕጻናትን ጨምሮ 40 ሰዎችን ትምህርት ቤት ውስጥ ገደለ።

ማፖውድዌ በተባለ አካባቢ በሚገኘው ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት ላይ በተፈጸመው ጥቃት፣ አብዛኞቹ ሟቾች ሕጻናት መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ በተጨማሪ 8 ሰዎች ለሕይወት አስጊ የሆነ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

በትምህር ቤቱ የተማሪዎች ማደሪያ ክፍል ውስጥ የነበሩ ወንድ ልጆች በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል ይገኛሉ።

ትናንት አርብ ለተፈጸመው ጥቃት መቀመጫውን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያደረገው አላይድ ዴሞክራቲክ ፎርስስ (ኤዲኤፍ) የተሰኘው ቡድን ተጠያቂ ተደርጓል።

አርብ እኩለ ሌሊት አካባቢ ጥቃቱ የደረሰበት ትምህርት ቤት እዚያው በአዳሪነት የሚኖሩ 60 ተማሪዎችን ያስተምራል።

የኡጋንዳ ፖሊስ ቃል አቀባይ ፍሬድ ኢናንጋ፣ የታጣቂ ቡድኑ አባላት የተማሪዎችን የማደሪያ ክፍሎችን በእሳት ካጋዩ በኋላ ምግብ ዘርፈዋል ብለዋል።

በጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ ልጆቹ በእሳት ተቃጥለው አልያም በስለት በአሰቃቂ ሁኔታ ተወግተው ተገድለዋል።

በተጨማሪም በትምህር ቤቱ የነበሩ አብዛኞቹ ሴቶች የሆኑ ልጆች በቡድኑ ተጠልፈው መወሰዳቸው ተነግሯል።

የጥቃቱ ሰለባዎች እድሜን በተመለከተ የአስካሁን ታወቀ ነገር የለም።

የተወሰኑት አስከሬኖች ክፉኛ በመቃጠላቸው ማንነታቸውን ለመለየት የዘረ መል ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ የተማሪዎቹ የሚተኙባቸውን ፍራሾች ያቃጠሉ ሲሆን፤ በአካባቢውም ቦምቦችን አፈንድተዋል።

በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያሉ ክፍሎች በእሳት ሲቃጠሉ የሚያሳዩ ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታይተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከተማሪዎቹ በተጨማሪ የአካባቢ ማኅብረሰብ አባላት ጨምር በጥቃቱ ሳይገደሉ አይቀርም የተባለ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ 40 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።

ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ተማሪ ያለበት ሁኔታ በዝርዝር ስላልታወቀ፣ የጥቃቱ ሰለባዎች እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አለ።

ጥቃቱን ተከትሎ የኤዲኤፍ ሽምቅ ተዋጊዎች ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ የሸሹ ሲሆን፣ የኡጋንዳ ጦር ታጣቂዎቹን እየተከታተለ ነው ተብሏል።

የኤዲኤፍ ሚሊሻ አባላት ሩዋንዳ እና ኡጋንዳን በሚያዋስነው ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ በአፍሪካ ትልቁ ቪሩንጋ ፓርክ ውስጥ መሸሸጋቸው ይታወቃል።

“ጦራችን ጠላትን ለማጥፋት እና የተጠለፉትን ለማስጣል እግር በእግር እየተከተላቸው ነው” በማለት የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ፌሊክስ ኩላዩግዬ ትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

የኡጋንዳ ጦር ሄሊኮፕተሮችን ጨምር ወደ ስፍራው በማሰማራት የታጣቂ ቡድን አባላቱን እያሳደደ ነው ተብሏል።

ከዚህ ቀደም ኡጋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይህን ታጣቂ ቡድን ለማጥፋት የጋራ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ነበር።

የታጣቂ ቡድኑ አባላት ትናንት አርብ ጥቃቱን ከማድረሳቸው በፊት ለሁለት ቀናት በኮንጎ እና ኡጋንዳ ድንበር አቅራቢያ ይገኙ እንደነበር የኡጋንዳ ደኅንነት ቢሮ መረጃ ነበረው ተብሏል።

ይህን ጥቃት የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት የኤዲኤፍ ሚሊሻ አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በአንዲት የኮንጎ መንደር ላይ ጥቃት ፈጽመው ከ100 ያላነሱ ሰዎች ወደ ኡጋንዳ ከተፈናቀሉ በኋላ ነው።

ጥቃቱ የተፈጸመበት ትምህርት ቤት ከኮንጎ ድንበር ሁለት ኪሎ ሜትር ብቻ ርቆ የሚገኝ ሲሆን፣ በኡጋንዳ ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ይህ ከ25 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

እአአ 1998 ላይ ይህ ታጣቂ ቡድን እንዲሁ ትምህር ቤት ላይ ባደረሰው ጥቃት 80 ተማሪዎች በመኖሪያ ክፍሎቻቸው ውስጥ በእሳት ተቃጥለው ሞተው ነበር። ከሟቾቹ በተጨማሪ 100 ተማሪዎች ተጠልፈው ተወስደው ነበር።

እራሱን አላይድ ዴሞክራቲክ ፎርስስ ብሎ የሚጠረው ቡድን የፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ መንግሥት ሙስሊሞችን ይጨቁናል በሚል እአአ 1990ዎቹ በምሥራቅ ኡጋንዳ ተመስርቶ ነው ጠመንጃ ያነሳው።

የኡጋንዳ እና የኮንጎ ጥምር ጦር በታጣቂ ቡድኑ ላይ ዘመቻ አካሂዷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኡጋንዳ እና የኮንጎ ጥምር ጦር በታጣቂ ቡድኑ ላይ ዘመቻ አካሂዷል።

መንግሥታዊ አሃዞች ከአጠቃላይ የኡጋንዳ ሕዝብ የሙስሊም ማኅብረሰብ ብዛት 14 በመቶ ነው ቢሉም፣ የኡጋንዳ የእስላምና ጠቅላይ ምክር ቤት አሃዙን ወደ 35 በመቶ ከፍ ያደርገዋል።

አንዳንድ የኡጋንዳ ሙስሊሞች በሃይማኖታችን ምክንያት በማኅበራዊ ሕይወት፣ በትምህርት እና በሥራ ቦታዎች ላይ መገለል ይደርስብናል ይላሉ።

እአአ 2001 ላይ ኤዲኤፍ በኡጋንዳ መንግሥት ከፍተኛ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ ዋና መቀመጫውን ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኪቩ ግዛት አዘዋውሮ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የትጥቅ ትግል እያደረገ ይገኛል።

የዚህ ቡድን መሥራች ጃሚል ማኩሉ እአአ 2015 ላይ በታንዛኒያ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ፣ ለኡጋንዳ ተላልፎ ተሰጥቶ በእስር ላይ ይገኛል።

ማኩሉን የተካው ሙሳ ሴካ ባሉኩ እአአ 2016 ላይ የሚመራው ቡድን የኢስላሚክ ስቴት አጋር መሆኑን አውጆ ነበር።

ይህ ቡድን እአአ 2021 ላይ በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃቶችን ስለማድረሱ ይገለጻል።