ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለግማሽ ክፍለ ዘመን ገላቸውን ያልታጠቡት ኢራናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
በመገናኛ ብዙኃን "የዓለማችን በጣም ቆሻሻው ሰው" ተብለው የሚጠሩት ግለሰብ ከብዙ አስር ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከታጠቡ በኋላ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
አሙ ሀጂ ገላዬን መታጠብ ያሳምምኛል በሚል ፍራቻ ሳሙና እና ውሃ ለመጠቀም አሻፈረኝ ሲሉ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አልፏቸዋል።
በደቡብ ፋርስ ግዛት ይኖሩ የነበሩት ኢራናዊው ቀደም ሲል የመንደራቸው ነዋሪዎች እንዲታጠቡ ያደረጓቸው ሙከራዎች ሳይቀበሉ ቆይተዋል።
የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት አሙ ሀጂ በመጨረሻ ጫና ሲበዛባቸው ከጥቂት ወራት በፊት ገላቸውን ታጥበው ነበር።
የኢራን የዜና ወኪል የሆነው አይአርኤንኤ የዜና ወኪል እንደዘገበው አዛውንቱ ገላቸውን እንደታጠቡ ብዙም ሳይቆዩ ታመው እሑድ ዕለት ህይወታቸው አልፏል።
እአአ በ2014 ለቴህራን ታይምስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ፖርኩፓይን የተባለ እንስሳ ስጋ እንደሚወዱ ተናግረዋል። ደጅጋህ በሚባል መንደር ጎረቤቶቻቸው በቀለሱላቸው አነስተኛ ቤት እንደሚኖሩም ገልጸዋል።
በወጣትነት ዘመናቸው ያጋጠማቸው “ስሜታዊ እንቅፋቶች” ለዚህ ላልተለመደው ያለመታጠብ ምርጫቸው እንዳበቃቸውም በጊዜው ገልጸዋል።
ለዓመታት ሰውነታቸውን አለመታጠባቸው ቆዳቸው በእድፍ እንዲሸፈን አድርጎታል ሲል አይአርኤንኤ ዘግቧል። ምግባቸው ደግሞ የበሰበሰ ሥጋ እና የሚጠጡት ደግሞ ንጽህና ያልተጠበቀ ውሃ እንደሆነ ዘግቦ ነበር።
አሙ ሃጂ ማጨስም ይወዱ ነበር። ከአንድ በላይ ሲጋራዎችን በአንድ ጊዜ ሲያጨሱ ታይተዋል።
እንዲታጠቡ ወይም ንጹህ የመጠጥ ውሃ ሊቀርብላቸው የተደረገው ሙከራ ግለሰቡን ያሳዝን እንደነበረ የዜና ወኪሉ ገልጿል።
ገላቸውን ሳይታጠቡ ለረዥም ጊዜ በመቆየት ክብረወሰን የመያዙ ጉዳይ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። አአአ በ 2009 አንድ ሕንዳዊ ለ35 ዓመታት ሳይታጠብ እና ጥርሱን ሳይፍቅ ስለመኖሩ ሪፖርቶች ነበሩ። ይህ ሕንዳዊ መጨረሻቸው ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም።