የአሜሪካና የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትሮች በስልክ ተወያዩ

ታትሟል

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን እና የሩሲያ አቻቸው ሰርጌይ ሾይጉ በስልክ ተወያዩ።

ሁለቱ መከላከያ ሚኒስትሮች በስልክ መወያየታቸው ‘ያልተጠበቀና ያልተለመደ’ ተብሏል።

ሎይድና ሾይጉ የስልክ ውይይቱን ያደረጉት ትናንት ዐርብ ዕለት ነበር።

ሁለቱም ወገኖች እንደተናገሩት የውይይታቸው ማጠንጠኛ ዩክሬን ነበረች።

ሁለቱ የመከላከያ ሚኒስትሮች ከግንቦት ወር ወዲህ መወያየት ሲችሉ የትናንቱ የመጀመርያቸው ነው።

የዐርብ ዕለቱን የስልክ ጥሪ ተከትሎ የፔንታገን የፕሬስ ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል ፓት ራይደር ለቢቢሲ እንደተናገሩት አሜሪካ ሁልጊዜም የውይይት በሮችን ክፍት አድርጋ ትቆያለች ብለዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ አሁን ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ የጸጥታ ስጋቶች በሁለቱ ሚኒስትሮች ውይይት ተደርጎባቸዋል፤ የዩክሬን ጉዳይም ተነስቷል ብሏል።

ከግንቦት ወር ውይይት ወዲህ የመጀመርያ ነው በተባለው በዚህ የስልክ ጥሪ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሚስተር ኦስቲን ለሩሲያው አቻቸው አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ስለመጠየቃቸው አልተሰማም።

ሚስተር ኦስቲን በግንቦት ወር በነበራቸው ንግግር ግን ሩሲያ የተኩስ አቁም እንድታደርግ ጠይቀው ነበር።

ይህ ውይይት ምናልባት ፑቲን በዩክሬን ላይ ኒክሊየር መሣሪያን መጠቀም ላይ እያሰቡበት ነው መባሉን ተከትሎ የተደረገ ነው።

ይሁንና አሜሪካም ሆነች አጋሯ ዩኬ እንደሚያምኑት ፑቲን ኒክሊየር የመጠቀም ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው ብለው ያምናሉ።

ይህ የሁለቱ ሚኒስትሮች የኒውክሊየር ስጋትን ተከትሎ የተደረገ ነው ወይ በሚል ለብርጋዲየር ጄኔራል ፓት ራይደር ጥያቄ ተነስቶላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ምንም እንኳ ፑቲን በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጡት ፍንጭ ኃላፊነት የጎደለውና አሳሳቢ ቢሆንም ሩሲያ ኒክሊየርን ጥቅም ላይ ታውላለች ለሚለው ያገኘነው ተጨባጭ ነገር የለም ብለዋል።

በአሜሪካና ሩሲያ መካከል የነበረው ግንኙነት ወትሮም የሻከረ ቢሆንም የዩክሬን ወረራን ተከትሎ ግን ይበልጡኑ ተበለሻሽቷል።

የሁለቱ አገራት መሪዎች በ2021 አጋማሽ ተገናኝተው የነበረና መገናኘታቸውም ለዓለም ሰላም ተስፋ የሰጠ የነበረ ቢሆንም የዩክሬን ወረራ ይህን ተስፋ አጨልሞታል።

የዩክሬን ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በነበሩ ወራት ፑቲንና ባይደን ተደጋጋሚ የስልክ ውይይቶችን አድርገው ነበር።

ይሁንና ወረራውን ተከትሎ ባይደን ለፑቲን ሥልጣን ሊለቁ ይገባል ማለታቸውን ተከትሎ ነገሮች ይበልጥ ሻክረዋል።

ወረራውን ተከትሎ ባይደንና ፑቲን ምንም ዓይነት ንግግር ኖሯቸው አያውቅም።

በሚቀጥለው ዓመት በኢንዶኒዥያ የብልጹግ-20 አገሮች ስብሰባ ላይ ሁለቱ መሪዎች የሚገኙበት ቢሆንም በሁለትዮሽ ለመነጋገር ግን ፍላጎት የላቸውም።

አሜሪካ ወረራውን ተከትሎ አሉ የሚባሉ ማዕቀቦችን ሩሲያ ላይ ያዘነበች ከመሆኗም ባሻገር ለዩክሬን ሰፊ ወታደራዊ እገዛን እየሰጠች ትገኛለች። ይህም የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ ወስዶታል።

ሩሲያ አካሌ ሆነዋል ባለቻቸው አራት የዩክሬን ክፍለ አገሮች አስቸኳይ ጊዜ ማወጇን ተከትሎ ጆ ባይደን በሰጡት አስተያየት ‘ፑቲን ዩክሬናዊያንን ለማንበርከክ ማስፈራራት ይዘዋል’ ብለው ነበር በቅርቡ።

 ቪላድሚር ፑቲን በበኩላቸው አሜሪካንና ምዕራቡን ባወገዙበት የቅርብ ጊዜ ንግግራቸው፥ ‘ምዕራቡ ዓለም ቅኝ ገዢነት ተጸናውቶታል’ ብለው ነበር።