አሜሪካዊቷ ለሰሜን ኮሪያዊያን 'ሪሞት' ሥራ በመስጠት ደሞዝ እንዲከፈላቸው በማድረጓ ክስ ቀረበባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ሕግ አንዲት አሜሪካዊት ለሰሜን ኮሪያዊያን የርቀት ሥራ እየፈለገች ደሞዛቸውን ሰሜን ኮሪያ ስትልክላቸው ነበር ሲል ከሷል።
ክሪስቲና ቻፕማን የተሰኘችው ግለሰብ እና ሌሎች ሰሜን ኮሪያዊያን የድርጊቱ ተሳታፊ በመሆናቸው ክስ ቀርቦባቸዋል።
ነዋሪነቷ አሪዞና የሆነው ግለሰቧ የአሜሪካ ዜጎችንን ማንነት እየሰረቀች ለውጭ ሀገር የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ትሰጥ ነበር፤ ሰዎች ደግሞ እኒህ ማንነቶችን ተጠቅመው አሜሪካዊ መስለው በአሜሪካ ኩባንያዎች ይቀጠሩ ነበር ይላል የአቃቤ ሕግ መዝገብ።
ክሪስቲና በዘጠኝ የተለያዩ መዝገቦች የአሜሪካ መንግሥት ለማራቆት ሠርታለች የሚል ክስ ቀርቦባታል።
አቃቤ ሕግ እንዳለው በማጭበርበር ሂደቱ የ60 ሰዎች ማንነት የተሰረቀ ሲሆን 7 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ ወደ ሰሜን ኮሪያ ተልኳል፤ ይህ ገንዘብ ሀገሪቱ ለምታካሂደው የጦር መሣሪያ ፕሮግራም ጥቅም ላይ ውሎ ሊሆን ይችላል።
300 የአሜሪካ ኩባንያዎች ስማቸው የተጠቀሰበት ይህ የማጭበርበር ሂደት በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2020 ነው የጀመረው የሚለው የክስ መዝገቡ "ሠራተኞች እጅግ የተካኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ናቸው" ይላል።
ስለማጭበርበሩ የማያውቁት ኩባንያዎች ተጭበርብረው እንደሆነ እስካሁን ያልተነገራቸው ቢሆንም አብዛኛዎቹ በጣም ግዙፍ የሚባሉ ድርጅቶች እና የቴሌቪዥን ኔትዎርኮች እንዳሉበት እንዲሁም አንድ የግል ወታደራዊ ተቋም እና ታዋቂ የመኪና አምራች እንደሚገኝበት ባለሥልጣናት ገልጠዋል።
የ49 ዓመቷ ክሪስቲና ከቤቷ ሆና የኮምፒውተር "እርሻ" በመዘርጋት ከኩባንያዎቹ የተሰጡ ላፕቶፖችን በመክፈት ሰሜና ኮሪያዊያኑ ሠራተኞች ልክ አሜሪካ ያሉ በማስመሰል ትሠራ ነበር ተብላለች።
57 ገፆች ያሉት የክስ መዝገብ እንደሚተነትነው ግለሰቧ የአይቲ ሠራተኞች ካሉበት ሆነው ከላፕቶፖቹ እንዲገናኙ በማድረግ ከኩባንያዎቹ ደሞዝ እንዲቀበሉ ታደርግ ነበር።
መዝገቡ አክሎ እንደሚገልጠው ግለሰቧ ለዚህ ሥራዋ "በየወሩ ከአይቲ ሠራተኞቹ ወርሃዊ ክፍያ የምትቀበል ሲሆን፤ ከማጭበርበር ሂደቱ ስታተርፍም ነበር።"
"ይሄ ክስ ከቤታቸው ሆነው የአይቲ ሥራ የሚሠሩ ሰዎችን ለሚቀጥሩ ኩባንያዎችና የመንግሥት ኤጀንሲዎች የማንቂያ ደወል ነው" ያሉት የፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ክፍል ኃላፊ ኒኮል አርጀንቲዬሪ ናቸው።
"እኒህ ወንጀሎች የሰሜን ኮሪያን መንግሥት ጠቅመዋል፤ የገቢ ምንጭ ሆነዋል፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አስፈላጊ መረጃዎች እንዲሾልኩ አድርገዋል" ሲሉ አክለዋል።
ባለሥልጣናት እንደሚሉት በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2020 ነው ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ክሪስቲና ቀርበው የኩባንያቸው "የአሜሪካ ተወካይ" እንድትሆን የጠየቋት።
ክሪስቲና ሰሜና ኮሪያዊ ዜግነት ካላቸው ጂሆ ሀን፣ ቹንጂ ጂን እና ሀዋራን ዡ ጋር የተከሰሰች ሲሆን ሰሜን ኮሪያዊያኑ እስካሁን በቁጥጥር ሥር አልዋሉም።
የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር እንደሚለው ሶስቱ ግለሰቦች ከሰሜን ኮሪያው መሥሪያ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ይህ ተቋም ባለስቲክ ሚሳዔል እና የጦር መሣሪያ ምርትን የሚቆጣጠር ነው።
ሚኒስቴሩ፤ የሰሜን ኮሪያን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና የፋይናንስ ማጭበርበርን በተመለከተ "መረጃ ለሚያቀብሉ" ሰዎች የ5 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ ለመክፈል ተዘጋጅቷል።
ክሪስቲና በቁጥጥር ሥር የዋለችው ባለፈው ሐሙስ አሪዞና ውስጥ ሲሆን የሚወክላት ጠበቃ ስለመቅጠሯ እስካሁን ግልፅ መረጃ የለም።












