ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጣሊያን የጠቅላይ ሚኒስትሯ የልብ ጓደኛን ጨምሮ ሦስት ሴቶች ካፌ ውስጥ ተገደሉ
በጣሊያን ሮም አንድ ግለሰብ በከፈተው የተኩስ እሩምታ ሦስት ሴቶች ተገደሉ።
ከሟቾቹ መካከል አንዷ የአዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ የልብ ወዳጅ ነበሩ።
የሮም ከንቲባ ሮቤርቶ ጓልቴሪ ድርጊቱን “ጭካኔ የተሞላበት’ ብለውታል።
ዛሬ ሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።
ተጠርጣሪው የ57 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን ድርጊቱን ለምን እንደፈጸመ የታወቀ ነገር የለም።
ሆኖም ሦስቱ ሴቶች የአካባቢ የነዋሪዎች ኮሚቴ አባላት የነበሩ ሲሆን ግለሰቡ ተኩስ ከመክፈቱ በፊት ከዚህ ኮሚቴ አባላት ጋር አምባጓሮ ፈጥሮ ነበር ተብሏል።
የነዋሪዎቸ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሉሲያና ቺዮርባ በዚህ ፊደኒ ሰፈር በሚገኝ ካፌ ውስጥ ሻይ ቡና እያሉ ነበር ብሏል፣ ላ ሪፐብሊካ ጋዜጣ።
ጥቃት አድራሹ ትናንት እሑድ “ሁላችሁንም እገድላችኋለሁ” እያለ ሲዝት ነበር ይላሉ የዓይን እማኞች።
ከዚያ ወዲያ ነው ከመቅጽበት ሽጉጥ አውጥቶ የተኩስ እሩምታ የከፈተው።
ፖሊስ ቦታው ከመድረሱ በፊት በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ተረባርበው ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር አውለውታል።
ከሦስቱ ሟቾች ሌላ ሁለት ሌሎች ሴቶች እና ሁለት ወንዶች ቆስለዋል። አንደኛው ለሕይወቱ አስጊ ሁኔታ ላይ ነው ያለው።
አዲሷ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆዮርጂያ ሜሎኒ እንዳሉት ከሟቾቹ አንዷ ባልንጀራቸው ነበረች።
ሜሎኒ ወዳጃቸውን በማጣታቸው የተሰማቸውን ሐዘን ከገለጹ በኋላ “እሷ ሁልጊዜም ቆንጆና ደስተኛ ሴት ነበረች” ሲሉ አክለዋል።
“ኒኮሌታ ልጆቿን ተንከባካቢ እናት፣ ልበ ቀና እና ሚስጥረኛ ጠንካራ ነገር ግን ሆደ ቡቡ ሴት ነበረች" ብለዋል ባሰፈሩት ማስታወሻ።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጨምረው ሟች ወዳጃቸው ኒኮሌታ “በቅርቡ ለ50ኛ ዓመት ልደቷ በገዛችው ቀይ ውብ ቀሚስ ደምቃ ነበር፤ ለኔ እስከዘላለሙ እንዲያ ቆንጆ ሆና በልቤ ትኖራለች” ብለዋል።
ፖሊስ ግለሰቡ በምን ተነሳስቶ ይህን ድርጊት እንደፈጸመ ለማወቅ ምርመራ ይዟል።
ይሁንና ድርጊቱ ከፖለቲካ ልዩነት ጋር የተያያዘ አይደለም እየተባለ ነው።
የጣሊያን ጋዜጦች እንደጻፉት ከሆነ ደግሞ ግለሰቡ ከነዋሪው ማኅበርተኞችና ከኮሚቴው ጋር እልህ ተጋብቶ ነበር፤ ምናልባት በብስጭት ተነሳስቶ የፈጸመው ግድያ ይሆናል ይላሉ።
ከሞሶሎኒ ወዲህ መጤ ጠል፣ ቀኝ አክራሪ፣ መንግሥት የመሠረቱት ጂዮርጂያ ሜሎኒ የጣሊያን የመጀመርያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ከወር በፊት ነበር።