ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ከሥልጣን እንዲለቁ በይፋ የጠየቁት የኤርትራ የቀድሞ ሚኒስትር በእስር ቤት አረፉ

የቀድሞው የገንዘብ ሚኒስትር  ብርሃነ አብርሃ

የፎቶው ባለመብት, Family

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሥልጣን እንዲለቁ በግልጽ የጠየቁት የቀድሞው የገንዘብ ሚኒስትር አቶ ብርሃነ አብርሃ በእስር ቤት ሳሉ ማረፋቸውን የቤተሰቡ አባላት ለቢቢሲ ትግርኛ አረጋገጡ።

የቀድሞው ሚኒስትር ከአምስት ዓመታት በፊት በኤርትራ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በማይታወቅ ስፍራው ከፍርድ ውጪ በእስር ቤት ሲማቅቁ ቆይተዋል።

የአቶ ብርሃነ ቤተሰቦች እንደገለጹት ሕይወቱ ማለፉን በተመለከተ መርዶ በመንግሥት አካላት በይፋ የተነገራቸው ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብራቸውንም በአሥመራ የአርበኞች መካነ መቃብር ለመፈጸም ታቅዷል።

ሆኖም ከኤርትራ መንግስት ስለሞቱም ይሁን ቀብሩ እስከ ኣሁን በይፋ የተሰማ ነገር የለም።

ብርሃነ የኤርትራን መንግሥት የምጣኔ ሀብት በተለይም በማዕድን ቁፋሮ ገቢው በኩል የሚታዩ ግልጽ ያልሆኑ አሰራሮችን በሰላ ሁኔታ የተቹ በሁለት ቅጽ የተከፈሉ “ሀገሬ ኤርትራ” (ሃገረይ ኤርትራ) የተሰኙ የፖለቲካ መጻህፍትን በውጭ አገር ማሳተማቸውን ተከትሎ ነበር በኤርትራ የደኅንነት ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ሆኖም አቶ ብርሃነ በእነዚህ በርካታ ዓመታት የእስር ቆይታቸው ፍርድ ቤት አልቀረቡም፣ ክስም አልተመሠረተባቸውም።

አቶ ብርሃነ በመጻህፍቶቻቸው በአገሪቱ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ትግበራ እንዲጀመር እና የኤርትራ ብሔራዊ ምክር ቤት (ፓርላማ) ሥራውን እንዲጀምርም ጥሪ አቅርበዋል።

የቀድሞው የገንዘብ ሚኒስትር ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ለኤርትራ ሕዝብ የተላከ እንደሆነ በተገለጸው የድምፅ መልዕክታቸው በሕይወት የተረፉትን የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት እንዲሰበሰቡ እና ፕሬዚዳንቱም ሥልጣን በሰላም እንዲለቁ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ሰለ አገሪቱ ያለፉ ዓመታት እና በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ በግልጽ መድረክ ውይይት እንዲደረግ ሃሳብ አቅርበው ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2001 ጂ-15 ተብለው የሚጠሩ የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ የባለሥልጣናት ቡድን ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።

ኤርትራ ከ27 ዓመታት በፊት ያጸደቀችው ሕገ መንግሥት ቢኖራት እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት (ፓርላማ) ከአውሮፓውያኑ 2002 ጀምሮ ለስብሰባ ተቀምጦ አያውቅም።

በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚመራው ገዢው ድርጅት ህዝባዊ ግንባር ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ (ህግደፍ) ሦስተኛ ጉባኤውን ያካሄደው ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ነው።

በተጨማሪም የአገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመጨረሻ ጊዜ ስብሰባ ያካሄደው በአውሮፓውያኑ 2011 ነበር።

ብርሃነ አብርሃ ማን ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኤርትራ ውስጥ በአውሮፓውያኑ 1945 የተወለዱት አቶ ብርሃነ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በኤርትራ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጂማ እንዲሁም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው ያጠናቀቁት።

በአውሮፓውያኑ 1972 ከአሜሪካው ኢሊኖይ ዩኒቨርስቲ በምጣኔ ሀብት እና በምህንድስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል። ከዚያም ከሦስት ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 1975 የኤርትራን የነጻነት የትጥቅ ትግልን ተቀላቅለዋል።

ለነጻነት በተካሄደው የትጥቅ ትግሉ ወቅት በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ማገልገላቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነጻነትዋን ከተቀዳጀች በኋላ በፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት የኤርትራ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤትም አባል ነበሩ።

አቶ ብርሃነ ከአውሮፓውያኑ 2001 አስከ 2012 የኤርትራ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በኤርትራ መንግሥት እጅ የሚገኘው ቢሻ የውርቅ ማዕድን ኩባንያ የገቢ ሪፖርት ላይ ግልጽነት የጎደለው አሠራር እንዳለ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጥያቄ በማንሳታቸው የተነሳ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ቆይተዋል።

ከአቶ ብርሃነ አብርሃ አራት ልጆች አንዱ የሆነው ኤፍሬም ከአራት ዓመታት በፊት ለቢቢሲ እንደተናገረው የአባቱ እስር መከራው ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን “ለቤተሰቦቻቸው እና ለጓደኞቻቸው ጭምር ተርፏል” ብሎ ነበር።

"አባቴን ሁል ጊዜ አስታውሳለሁ፤ ነገር ግን የት እንዳለ አላውቅም። በሕይወት ይኑር ወይም አይኑር አላውቅም” ሲልም በወቅቱ ለቢቢሲ ገልጿል።

አክሎም “በእኔ፣ በወንድሞቼ እና በአፍቃሪዋ እናቴ ላይ የደረሰውን ሐዘን መግለጽ አልችልም። የአባቴ መታሰር ለእኔ የማያቋርጥ ህመም ነው” ሲል አስረድቶ ነበር።

በአሜሪካ አገር ነዋሪ የሆነው ኤፍሬም እሱ ራሱ በኤርትራ በተለያዩ እስር ቤቶች ለስድስት ወራት በእስር ላይ ቆይቷል።

እንደ ዕድል ሆኖ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ፣ በድብቅ ጠፍቶ ስቃይ በሞላበት ረዥም ጉዞ ከኤርትራ መውጣቱን ተናግሮ ነበር።