የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ካንዬ ዌስት “ሳትጠራ እና ሳታሳውቅ” መጥተሃል ተብሎ ከስኬቸርስ ቢሮ እንዲወጣ ተደረገ

ካንዬ ዌስት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ስኬቸርስ የተባለው የጫማ አምራች ኩባንያ ራፐሩ ዬ፣ በቀድሞ ስሙ ካንዬ ዌስት፣ “ሳያሳውቅ እና ሳይጋበዝ” መጥቷል በሚል ከኩባንያው ሕንጻ እንዲወጣ እንዳደረገው ገለፀ።

ድርጅቱ አክሎም ከራፐሩ እና ዲዛይነሩ ዬ ጋር በጋራ የመስራት “ምንም ዓይነት ፍላጎት” የለኝም ብሏል።

ይህ ዜና የተሰማው የጀርመኑ ስፖርት ትጥቅ አምራች አዲዳስ፣ ዬ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሰጠውን ፀረ አይሁዳዊ አስተያየት ተከትሎ ያለውን ግንኙነት ካቋረጠ በኋላ ነው።

ቢቢሲ የዬን ወኪሎች አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

ስኬቸርስ በመግለጫው ዬ በቢሮው ከሌሎች ጋር ሆኖ ከመጣ በኋላ “ያልተፈቀደ የፊልም ቀረጻ በማድረግ ላይ ነበር” ብሏል።

አብረውት መጥተው ከነበሩ ሰዎች ጋርም የተወሰነ ንግግር ከተደረገ በኋላ ሕንጻውን ለቅቀው እንዲወጡ መደረጉን ጨምሮ ገልጿል።

ኩባንያው አክሎም “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚሰጣቸውን ከፋፋይ ሀሳቦች የምንቃወም ሲሆን የፀረ አይሁዳዊ ወይንም ማንኛነውንም ዓይነት የጥላቻ ንግግሮች አንታገስም” ብሏል።

በተጨማሪም “በድጋሚ አጽንኦት መስጠት የምንፈልገው ዌስት የመጣው ሳያሳውቅ እና ሳይጠራ ነው” ብሏል።

ዬ የባይ ፖላር ዲዝኦርደር ታማሚ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልልቅ ስም ካላቸው ድርጅቶች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ እየገባ ያለው የስራ ውል እየተቋረጠ ይገኛል።

እነዚህ እርምጃዎች የዬን ገቢ ክፉኛ የሚጎዱት ሲሆን በቅርቡም ከፎርብስ የቢሊየነሮች ዝርዝር ስር ስሙ እንዲወጣ ሆኗል።

መጽሔቱ ዬ ከአዲዳስ ጋር ያለው የስራ ውል በመቋረጡ ብቻ ካለው አጠቃላይ የ1.5 ቢሊየን ዶላር ሀብት ወደ 400 ሚሊዬን ወርዷል ሲል አስፍሯል።

ማክሰኞ ዕለት አዲዳስ ከዬዚ ብራንድ ጋር ያለውን ትብብር “የፀረ አይሁዳዊ እንዲሁም የትኛውም ዓይነት የጥላቻ ንግግርን አንታገስም” በማለት ውሉን ማቋረጡ ይታወሳል።

አዲዳስ አክሎም ከአሁን ጀምሮ ምርቶቹ ከገበያ አንዲወጡ ይደረጋል ሲል አስታውቋል።

ባለፈው ወር በፓሪስ የፋሽን ሳምንት ላይ “ኋይት ላይቭስ ማተር “ የሚል ቲሸርት ለብሶ በመገኘቱ አዲዳስ ጉዳዩን ማጤን ጀምሮ ነበር።

ከቀናት በኋላም ራፐሩ በትዊተር ገፁ ላይ ፀረ አይሁዳዊ መልዕክት ያለው ጽሁፍ በማስፈሩ ወዲያው ከማህበራዊ ሚዲያው ታግዷል።

ከዚህ ቀደምም የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ካንዬ ዌስት በታዋቂው ኮሜዲያን ትሬቨር ኖዋ ላይ በሰነዘረው ዘር ተኮር ስድብ ምክንያት ከኢንሰታግራም ለ24 ሰዓታት ታገዶ ነበር።

አዲዳስ ተወዳጅ ከሆነው ዬ ብራንድ ጋር ያለውን ስምምነት በመሰረዙ ብቻ እኤአ በ2022፣ 217 ሚሊየን ፓውንድ ይከስራል።