የጋዛ ሐኪሞች የእስራኤል ጥቃት ተጎጂዎችን ለማከም ከአቅማችን በላይ ነው አሉ

አስከሬን የያዙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ሰዎች አስከሬን በአል ሽፊ ሆስፒታል ቀብር እየተፈፀመ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በጋዛ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ብቸኛ ሆስፒታል ሐኪሞች በእስራኤል ጥቃት የቆሰሉ ሰዎችን በሕክምና ግብዓት እጥረት እና በማይመች ሁኔታ ማከም ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ተናገሩ።

በአል ሽፋ ሆስፒታል የበጎ ፈቃድ ሐኪም የሆኑት አንድ አውስትሪሊያዊ ሐኪም በየቀኑ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እንደሚያልፍ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ በቅርቡ ሕይወቷ ካለፈ ነፍሰ ጡር እናት የአንድን ጨቅላ ሕፃን ሕይወት እንዴት እንዳተረፉ በመግለፅ የሁኔታውን አስከፊነት አስረድተዋል።

የእስራኤል ኃይሎች የምድር እንቅስቃሴያቸውን በማስፋት የሐማስ ጠንካራ ይዞታ ናት የሚሏትን የጋዛ ከተማን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፤ ከሆስፒታሉ በ500 ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኙም ተነግሯል።

የዓይን እማኞች ታንኮች ከከተማዋ ደቡብ እና ሰሜን ምዕራብ ክፍል ወደ መሀል ከተማ እየተመሙ ነው ብለዋል።

የእስራኤል የአየር፣ የከባድ መሳሪያ፣ የድሮን እና ፈንጅ የታጠቁ ተሽከርካሪዎች የሚያደርሷቸው ጥቃቶች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያንን በየቀኑ ከቤታቸው እያፈናቀሉ ነው።

በጋዛ ሰርጥ ትልቁ የሕክምና ማዕከል የሆነው አል ሻፋ ሆስፒታል ከ23 ወራት ጦርነት በኋላ በፍርስራሽ የተሞላ፣ በጉድጓዶች የተከበበ እና በእሳት በተቃጠሉ ክፍሎች እና በጥይት ቀዳዳዎች የተሞላ ሆኗል።

በዚህ ሆስፒታል እያገለገሉ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፤ አብዛኞቹ አልጋዎች ፍራሽ እንደሌላቸው፣ የመድኃኒቶች እጥረት እንደገጠማቸው እና የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

የድንገተኛ ክፍል ባለሙያ የሆኑት አውስትሪሊያዊ በጎ ፈቃደኛ ዶ/ር ናዳ አቡ አልረብ "የጅምላ ግድያ ነው። ሞት፣ መሰቃየት፣ ቅዠት" ሲሉ ሁነቱን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በርካታ ቁስለኛ ታካሚዎች ያለ ማደንዘዣ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት መገደዳቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት አንገቷ ከተቆረጠ የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር እናት ድንገተኛ ቀዶ ሕክምና በማድረግ የሕፃኗን ሕይወት ማትረፍ እንደቻሉ ገልፀዋል።

ዶ/ር ሳያ አዚዝ የተባሉ ሌላ ባለሙያም የሁኔታውን አሳሳቢነት ሲገልፁ የሆስፒታላቸው የአጥንት ቀዶህክምና ባለሙያዎች ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጧቸው ታካሚዎች በመኖራቸው እጅ እና እግሩ የተሰበሩ የስድስት ዓመት ሕፃን ሕክምና ለማግኘት ሦስት ቀናት መጠበቁን ገልፀዋል።

"በየሁለት ሰዓቱ በርካታ ከባድ ቁስለኞች በሕይወት እና ሞት መካከል ሆነው ይመጣሉ። መኖር ወይም አካለ ጎደሎ መሆን ምርጫ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በየአልጋዎች የፈሰሰ ደም አለ። ምንም ቁሳቁስ የለም። ምትክም የለም። የጤና ባለሞያዎችን ሐዘን እና ልብ ስብራት ማየት ይቻላል" ሲሉም ጫናውን ገልፀዋል።

ባለፈው ወር እስራኤል ጥቃቷን እንደምታጠናክር ከማሳወቋ በፊት አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስልጤማዊያን በጋዛ ከተማ ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።

ከዚህን ጊዜ ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 320 ሺህ የሚሆኑ የከተማይቱ ነዋሪዎች ወደ ደቡባዊ አካባቢ መሰደዳቸውን ሲያሳውቅ፤ የእስራኤል ጦር ግን ይህን ቁጥር 640 ሺህ ያደርሰዋል።

የእስራኤል ጦር ነዋሪዎች ሕክምና፣ የምግብ እና የውሃ አቅርቦት ተዘጋጅቷል ብሎ በለየው አል ማዋሲ ደቡባዊ የከተማዋ አካባቢ እንዲሸሹ ማሳሳቢያ ሰጥቷል።

ይሁን እንጂ የዓይን እማኞች ወደ አካባቢው የሚወስደው መንገድ በመጨናነቁ ስፍራው ላይ ለመድረስ ሰዓታትን እንደሚወስድ ተናግረዋል።

ከአካባቢው ሰዎችን የማስወጣት ዋጋ በቤተሰብ ሦስት ሺህ ዶላር መድረሱ የተነገረ ሲሆን፤ ለአብዛኞቹ ቤተሰቦች ከአቅም በላይ እንደሆነ ይታመናል።

የመንግሥታቱ ድርጅት በአል ማዋሲ መጠለያ የተዘጋጁ ድንኳኖች ከአቅማቸው በላይ ተፈናቃይ መያዛቸውን እና ደኅንነታቸው የማያስተማምን መሆኑን ገልጿል።