ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚያገናኟትን መንገዶች በሙሉ እንደምትዘጋ ሰሜን ኮሪያ አስታወቀች
ሰሜን ኮሪያ ከረቡዕ፣ መስከረም 29/ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚያገናኟትን የመኪና እና የባቡር መስመሮችን በማቋረጥ ሁለቱን አገራት “ሙሉ በሙሉ ለመለያየት” መወሰኗን ገለጸች።
"ደቡባዊው ድንበር በዘላቂነት ይዘጋል" ያለው የአገሪቱ ጦር፤ በራሱ ድንበር በኩል ያሉ ቦታዎችን ጥበቃ እንደሚያጠናክር አስታውቋል።
በደቡብ ኮሪያ ውስጥ የሚደረጉ የጦርነት ልምምዶች እና የአሜሪካ የኒውክሌር ንብረቶች በአከባቢው በተደጋጋሚ መገኘታቸውን በመግለጽ እርምጃውን "ጦርነትን ለመግታት ራስን የመከላከል እርምጃ" ሲል የኮሪያ ህዝብ ጦር (ኬፒኤ) ገልጾታል።
ውሳኔው በኮሪያ መካከል ያለው ውጥረት ከዓመታት በኋላ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት ያለውን ፍጥጫ መባባሱን ያሳያል።
“በኮሪያ ግዛት ላይ ያለው አስቸኳይ ወታደራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮሪያ ኃይሎች የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነትን በብቃት ለመጠበቅ የበለጠ ቆራጥ እና ጠንካራ እርምጃ እንዲወስዱ ይጠይቃል” ሲል ኬፒኤ በመንግስታዊው መገናኛ ብዙሃን ኬሲኤንኤ በኩል አስታውቋል።
መግለጫው በአብዛኛው የፒዮንግያንግ የይስሙላ እርምጃ ነው።
ቀደም ብሎም ቢሆን ከሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ የሚወስዱ መንገዶች እና የባቡር ሃዲዶች እምብዛም ጥቅም ላይ አይውሉም።
መስመሮቹም በሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ባለፈው ዓመት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲፈርሱ ተደርገዋል።
ውሳኔው ከደቡብ ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድትቀይር በፒዮንግያንግ ላይ ሰፊ ግፊት በጨመረበት እና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ያበላሹ በርካታ ቀስቃሽ ክስተቶችን ተከትሎ የመጣ ነው።
ከሚሳዔል ሙከራዎች እስከ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቆሻሻ ፊኛዎችን በሰሜን ኮሪያ ደቡባዊ ድንበር በኩል እስከ መላክን የሚያካትቱ ክስተቶች ተፈጥረዋል።
በተለይም የሰሜን ኮሪያው ገዥ ኪም ጆንግ ኡን እአአ በ2023 መጀመሪያ ላይ ከደቡብ ጋር ለመዋሃድ እየጣሩ እንዳልሆኑ አስታውቀዋል። ይህም በኮሪያ ግዛቶች ጦርነት ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
በጥር ወር በተካሄደው የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ የሕዝብ ምክር ቤት (ኤስፒኤ) ስብሰባ ላይ "የአገራችንን አንዳንድ ህገ መንግስታዊ ይዘቶች ማሻሻል አስፈላጊ ይመስለኛል" ብለዋል ኪም።
"በእኔ ዕይታ በህገ መንግስቱ ውስጥ እንደ 'ሰሜናዊ አጋማሽ' እና 'ነጻነት፣ ሠላማዊ መደመር እና ታላቅ አገራዊ አንድነት' የሚሉ አገላለጾች መሰረዝ አስፈላጊ ነው" በማለት ህገ መንግስቱን "በሚቀጥለው ስብሰባ" መከለስ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ቀጣዩ ስብሰባ በዚህ ሳምንት ተካሂዶ ማክሰኞ ዕለት ተጠናቋል። ኪም ቀደም ብለው የሰጡትን አስተያየት ፒዮንግያንግ ተግባራዊ አድርጋ በውህደት እና በድንበር ፖሊሲዎች ላይ የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን ታደርጋለች ሲሉ ብዙዎች ቢጠብቁም ምንም ዓይነት ለውጦች ስለመኖራቸው ይፋ አልተደረገም።
በኮሪያ ኢንስቲትዩት ፎር ናሽል ዩኒፊኬሽን የሚሠሩ አንድ ተንታኝ ፒዮንግያንግ ተጨባጭ ውሳኔ ከማስተላለፏ በፊት የአሜሪካን የምርጫ ውጤት ልትጠብቅ እንደምትችል ጠቁመዋል።
ባለሥልጣናቱ “የህገ መንግሥት ማሻሻያዎችን ከአዲሱ (የአሜሪካ) አስተዳደር አቅጣጫ ጋር ለማጣጣም ያስቡበታል” ሲሉ ሆንግ ሚን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
አገሪቱ ከደቡብ ጋር የሚያገናኟትን ሁሉንም መስመሮች ለመቁረጥ የወሰደችው ውሳኔ በኤስፒኤ ስብሰባ ስለመወሰኑ ግልጽ አይደለም።