የሞቃዲሾ ፖሊስ አዛዥ በአልሻባብ በተጠመደ ቦምብ ተገደሉ

ኮሚሽነር ፋርሃን ሞሐሙድ አዳ

የፎቶው ባለመብት, Farhan Mohamoud Adan/fb

የምስሉ መግለጫ, ኮሚሽነር ፋርሃን ሞሐሙድ አዳ
ታትሟል

የሶማሊያ ዋና ከተማ የሞቃዲሾ ፖሊስ ኮሚሽነር ፋርሃን ሞሐሙድ አዳን በታጣቂው ቡድን አልሻባብ መንገድ ዳር በተጠመደ የቦንብ ፍንዳታ ተገደሉ።

ፋርሃን ቃራሌ በሚል ተጨማሪ ስም የሚታወቁት የፖሊስ ኮሚሽነሩ አርብ ዕለት ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ በስተሰሜን 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባልኣድ ወረዳ አቅራቢያ ነው በተጠመደ ቦምብ የተገደሉት።

ኮሚሽነሩ በፖሊስ ተሽከርካሪዎች ታጅበው ሲጓዙ ነበር ታጣቂው አስላማዊ ቡድን አልሻብብ አጥምዶታል በተባለ ቦምብ መኪናቸው የተመታው።

ታጣቂ ቡድኑ የታችኛው እና የመካከለኛው ሸበሌ ክልሎችን ከምታገናኘው ባስራ ከተባለችው ቁልፍ መንደር ለቆ ከመውጣቱ በፊት ቦምቡን ሳያጠምደው እንዳልቀረ ተነግሯል።

የፖሊስ ኮሚሽነሩ ፋርሃን ቃሮሌ፣ ሞቃዲሾ የምትገኝበት ባናዲር ክልል ፖሊስ ኃይል አዛዥ ከመሆናቸው ቀደም ብሎ የሶማሊያ ልዩ የፖሊስ ኃይል አዛዥ ነበሩ።

የፖሊስ አዛዡ ባለፈው ግንቦት ወር እና ቀደም ባለው ዓመት ሐምሌ ወር ከተሞከሩባቸው ሁለት የግድያ ሙከራዎች ተርፈዋል።

ከፍተኛ የፖሊስ ኃላፊውን ግድያ በተመለከተ የአሁኑ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ፣ የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ እና ሌሎች የሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣንት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።   

በፖሊስ ኮሚሽነሩ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ከዚህ ወር መጀመሪያ አንስቶ በሂራን ክልል የሚገኝ የጎሳ ሚሊሻ በሶማሊያ መንግሥት እና ሠራዊት ድጋፍ በአልሻባብ ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ነው። በዚህም ሚሊሻዎቹ የሂራን ክልልን ከታጣቂው ቡድን አስለቅቀው ለመቆጣጠር ችለዋል።

አልሻባብ በደቡብ እና በማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ ሰፊ አካባቢን ተቆጣጥሮ ቢቆይም፣ ቡድኑ ከሞቃዲሾ ከወጣ በኋላ አሁን በተከፈተበት የተቀናጀ ጥቃት ምክንያት ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ ይዞታዎቹን እያጣ ነው።

አርብ ዕለት የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዲካዲር ሞሐመድ ኑር፣ ለአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ሠራዊቱ ከየአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር በታችኛው የሸበሌ ክልል ውስጥ ያሉ ባስራን ጨምሮ ዘጠኝ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።