በደቡብ ኮርያ የሀሎዊን በዓል በአደባባይ ሲከበር በደረሰ አደጋ ቢያንስ 151 ሰዎች ሞቱ

የተጎዱት ሰዎች
ታትሟል

በደቡብ ኮርያ የሀሎዊን በዓል ለማክበር የወጡ ሰዎች በገጠማቸው አደጋ ቢያንስ 151 የሚደርሱት ሕይወታቸው አልፏል። 82 ሰዎች ደግሞ ተጎድተዋል።

በመዲናዋ ሴዑል በሚገኝ ጠባብ አደባባይ ላይ በዓሉን ለማክበር የወጡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነበር።

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወዲህ ያለ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የተካሄደ የመጀመሪያው የአደባባይ ክብረ በዓል ነበር።

የሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ስለነበር መገፋፋትና መረጋገጥ መከሰቱ ተዘግቧል።

ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሲሆን፤ 19ኙ የውጭ አገር ዜጋ ናቸው።

አደጋው በምን ምክንያት እንደተከሰተ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

አስቸኳይ ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ የደቡብ ኮርያ ፕሬዝዳንት ዮን ሱን-ዮል የተጎዱትን የሚያክም ግብረ ኃይል አቋቁመዋል።

እአአ ከ2014 ወዲህ በአገሪቱ የተከሰተ የከፋ አደጋ ነው ተብሏል። ያኔ ስዑል የተባለ መርከብ ሰጥማ 300 ሰዎች ሞተዋል።

ሀሎዊን የተከበረበት ኢታዎን የተባለው ሰፈር በምሽት ሕይወት ዝነኛ ነው።

በተለይ ቅዳሜና እሑድ አገሬውና ጎብኚዎች ያዘወትሩታል።

ሀሎዊን በደቡብ ኮርያ ብዙ ሰው ወደ አደባባይ ከሚወጣባቸው ቀኖች መካከል ነው።

ትላንትም በዓሉን ለማክበር 100,000 በቦታው ተገኝተው እንደነበር ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአንድ የተጨናነቀ መንገድ ላይ መገፋፋቱ እንደተጀመረ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ቪድዮዎች አሳይተዋል።

መንገዱ እጅግ ጠባብ ሲሆን፣ በቦታው የነበሩ ሰዎች በርካታ ነበሩ።

አንድ ቪድዮ ሰዎች መተንፈስ ተቸግረው ያሳያል።

ሰዎች በሰዎች ላይ ተደራርበውም ይታያል። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አስክሬኖች ሲያወጡ የሰዎች ለቅሶና ሲቃም ይሰማ ነበር።

የተወሰኑ ሰዎች አስክሬን ወደ አምቡላንስ ሲወሰድ፣ የተቀሩት አስክሬን በፕላስቲክ ተሸፍኖ መንገድ ዳር ተቀምጦ ታይቷል።

ራሳቸውን የሳቱ ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ ትንፋሽ በመስጠት ሲሞክሩ የነበሩም አሉ።

ከመላው አገሪቱ በመቶች የሚቆጠሩ የአደጋ ሠራተኞች ናቸው በቦታው የተገኙት።

የሞቱትን ሰዎች አስክሬን ቤተሰቦቻቸው እንዲወስዱ የሚደረግ ሲሆን፤ የሟቾች ቁጥር በርካታ በመሆኑ ሂደቱ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተገልጿል።

አደጋው ሲከሰት የ30 ዓመቷ ጂዎን ጋውል ከጓደኞቿ ጋር እየጠጣች እንደነበር ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ነግራለች።

“ሰዎች መጎዳታቸውን ጓደኛዬ ስትነግረኝ ደንግጬ ከመጠጥ ቤቱ ወጣሁ። መንገድ ላይ ራሳቸውን ለሳቱ ሰዎች ትንፋሽ የሚሰጡ ሰዎች አየሁ” ብላለች።

በቦታው የነበረ ዶክተር እንዳለው፣ መጀመሪያ ላይ ለተወሰኑ ሰዎች ትንፋሽ በመስጠት ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሞክር ነበር። ቆይቶ ግን ራሳቸውን የሳቱ ሰዎች ቁጥር እየናረ ሄዷል።

አካባቢው መጨናነቁን ያዩ ሰዎች አደጋ ሊገጥም እንደሚችል የሚጠቁሙ ጽሑፎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲጽፉ ነበር።

ፓርክ የንግ-ሁን የተባለ የዓይን እማኝ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንዳለው፣ ለገና እና ሌሎች በዓሎች ከሚሰበሰቡ ሰዎች የበለጠ ነበር የወጣው።

የአደባባይ በዓሎች እና የሰዎች ደኅንነትን የተመለከቱ ፖሊሲዎች እንዲከለሱ ውሳኔ ተላልፏል።

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የአውሮፓ ኅብረት ዲፕሎማት ጆሴፕ ቦሬል እና የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱልቪን የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።