የዩናይትድ ኪንግደም ቱጃር ቤተሰብ አባላት በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ ቀረበባቸው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩናይትድ ኪንግደም ቱጃር ቤተሰብ አራት አባላት በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በጉልበት ብዝበዛ ክስ ቀረበባቸው።
47 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት ያለው የሒንዱጃ ቤተሰብ፣ ከቤት ሠራተኞች ይልቅ ውሻቸውን ለመንከባከብ ብዙ ገንዘብ አውጥተዋል በሚል በስዊትዘርላንድ ተከሰዋል።
በጀኔቫ የሃብታሞች ሰፈር በሆነው ኮሎግንይ ቅንጡ ቪላ ቤት ባለቤት በሆነው በዚህ ቤተሰብ ላይ የቀረቡት አብዛኞቹ ክሶች ልጆቻቸውን እና ቤታቸውን የሚጠብቁላቸውን ሠራተኞች ከሕንድ ከማስመጣት ልምዳቸው ጋር የተያያዙ ናቸው።
ፓራካሽ እና ካማል ሒንዱጃ እንዲሁም ከወንድ ልጃቸው እና ባለቤታቸው ናምራታ ጋር በመሆን የሠራተኞቻቸውን ፓስፖርት በመንጠቅ፣ ለ18 ሰዓታት ሥራ ከስምንት ዶላር ያነሰ በመክፈል እና ከቤት በነጻነት እንዳይወጡ በመከልከል ነው ክሱ የቀረበባቸው።
ምንም እንኳን ከጉልበት ብዝብዛ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ባለፈው ሳምንት እልባት ቢያገኝም፣ቤተሰቡ በስዊትዘርላንድ ከባድ ወንጀል በሆነው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ የፍርድ ሒደት ላይ ይገኛል።
ግለሰቦቹ ግን ድርጊቱን አልፈፀምንም ብለዋል።
በዚህ ሳምንት በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ በጀኔቫ ከሚታወቁ አቃቤ ሕጎች አንዱ የሆኑት ይቭስ ቤርቶሳ፤ ይህ ቤተሰብ ከሠራተኞቹ ክፍያ ይልቅ ውሻቸውን ለመንከባከብ በዓመት 10 ሺህ ዶላር እንደሚያወጣ በመግለጽ በሠራተኞች ላይ የሚፈፀመውን የጉልበት ብዝበዛ በንጽጽር አስረድተዋል።
የቤተሰቡ ጠበቆችም ከሠራተኛ ዝቅተኛ ክፍያ ጋር በተያያዘ የቀረበውን ክስ በቀጥታ ባይክዱም፣ ሠራተኞቹ የምግብ እና የመኝታ አገልግሎት በነጻ እንደሚያገኙ በመጥቀስ ጉዳዩ በአውዱ መሠረት መታየት እንዳለበት ተናግረዋል።
ሠራተኞችን ብዙ ሰዓት ማሰራትም በፍርድ ቤቱ አከራካሪ የነበረ ሲሆን አንድ ተከላካይ ጠበቃ፤ ከሒንዱጃ ልጆች ጋር ፊልም ማየት ሥራ አይደለም ሲሉ ክሱን አጣጥለዋል።
የተወሰኑ የቀድሞ የሒንዱጃ ሠራተኞችም ቤተሰቡ ተግባቢ እና ሠራተኞቹን በክብር የሚይዝ እንደሆነ ለቤተሰቡ ምስክርነት ሰጥተዋል።
ሆኖም የሠራተኞቻቸውን ፓስፖርት በመቀማት ያለ ፈቃድ ከቤት መውጣት እንዳይችሉ አድርገዋል የሚለው ክስ ከባድ ሲሆን በሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሊጠየቁበት ይችላሉ።
በዚህም ግለሰቦቹ የእስር ቅጣት እና ሚሊዮን ዶላሮች ካሳ እንዲሁም የሕግ ክፍያ እንዲከፍሉ አቃቤ ሕግ በርቶሳ ጠይቀዋል።
የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የዓለም ቱጃሮች መናገሻ በሆነችው ጀኔቫ፣ከቤት ሠራተኞች አያያዝ ጋር የተገናኘ ክስ ሲቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
እንደ አውሮፓውያኑ 2008 የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሞአመር ጋዳፊ ልጅ ሃኒባል ጋዳፊ፣ እርሱ እና ባለቤቱ ሠራተኞቻቸውን ደብድበዋል በሚል ክስ በጀኔቫ በሚገኘው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሉ ታስሮ ነበር።በኋላ ላይ ግን ክሱ ተቋርጧል።
ይህም በስዊትዘርላንድ እና በሊቢያ መካከል የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሻክሮ ነበር። የአጸፋ ምላሽ ለመስጠትም ሁለት የስዊዝ ዜጎች በትሪፖሊ ታስረው ነበር።
ባለፈው ዓመት ደግሞ አራት ፊሊፒናውያን የቤት ሠራተኞች ለአራት ዓመታት ለሰራንበት አልተከፈለንም ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ የጀኔቫ ዲፕሎማት በሆኑ ግለሰብ ላይ ክስ ከፍተዋል።












