ጃፓን ርእደ መሬት፡ የ90 ዓመት አዛውንት ከ5 ቀን በኋላ ፍርስራሽ ውስጥ በሕይወት ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
በጃፓን ርዕደ መሬት ከ5 ቀናት በኋላ አንዲት የ90 ዓመት አዛውንት በፍርስራሽ ውስጥ በሕይወት ተገኙ።
ሴትዮዋ በሕይወት የተገኙት በሱዙ ከተማ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንጻ ፍርስራሽ ሥር ነው።
የጃፓን የሰሞኑ ርእደ መሬት በሬክተር መለኪያ 7.5 የተመዘገበ ነው። መሬት መንቀጥቀጡ በባሕር ዳርቻ የተከሰተ ይሁን እንጂ ሩቅ ያሉ ባሕረ ገብ ከተሞችን ጭምር አፈራርሷል።
በዚህ ርእደ መሬት 120 ሰዎች ሞተዋል። ከ200 በላይ ደግሞ የገቡበት አልታወቀም።
የነፍስ አድን ሠራተኞች በተመሳሳይ ቦታ ሌላ የ40 ዓመት ሴት በሕይወት ማግኘታቸው ተዘግቧል።
በእንዲህ ዓይነቱ የነፍስ አድን ሥራ የመጀመርያዎቹ 72 ሰዓታት ወሳኝ የሚባሉ ናቸው። ከዚያ ወዲያ ባሉ ቀናት ሰው በሕይወት የመኖሩ ነገር በተአምር ካልሆነ የሚታሰብ አይደለም።
እነዚህ ሁለት ሴቶች የተገኙት ከ5 ቀናት በኋላ መሆኑ ጉዳዩን አነጋጋሪ አድርጎታል።
የጃፓን ነፍስ አድን ሠራተኞች ሩቅ የሚገኙና በመንገድ መዘጋት ምክንያት ሊደረስባቸው ላልቻሉ ቀበሌዎች በሄሊኮፕተር እርዳታ እያደረሱ ነው።
ጉዳቱ በደረሰባቸው ቀበሌዎች ከ30ሺህ በላይ ሰዎች መንግሥት ባዘጋጃቸው መጠለያ ጣቢያዎች ነው የሚገኙት።
ከቅዳሜ ጀምሮ 23ሺህ የመሆኑ ቤተሰቦች ያለ መብራት በጨለማ ነው ያሉት። ከ66ሺህ አባወራዎች በላይ ያለ ቧንቧ ዉሃ ነው ኑሮን እየገፉ ያሉት።
የኢሻካዋ ገዥ ሂሮሺ ሐሴ የተቋረጡት የመብራትና የዉሃ አገልግሎቶችን ለመመለስ ዘለግ ያለ ጊዜን ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል።
አንዳንድ ሆስፒታሎች ጭምር ዉሃና መብራት እያገኙ አለመሆኑ በዚያ ለሚገኙ ታማሚዎች መጥፎ ዜና ሆኗል።
ጃፓን ለርእደ መሬት የተጋለጠች አገር ስትሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ከ500 ያላነሱ መጠነኛና አነስተኛ መሬት መንቀጥቀጦች መከሰታቸው ተዘግቧል።












