የሶማሊያ ፓርላማ የቀደሞውን የአልሸባብ መሪ ሹመት አጸደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሶማሊያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀደሞው የአልሸባብ ታጣቂ ብድን ቃል አቃባይ የተካተተበትን የካቢኔ ሹመት ማጽደቁን የአገሪቱ የዜና ወኪል ሶና ዘግቧል።
የአልሸባብ አመራር የነበሩት ሙክታር ሮቦው የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ባለፈው ማክሰኞ ነበር የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ቤሪ የገለጹት።
ሰውየው እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 ከአልሸባብ የኮበለሉ ሲሆኑ በቀደሞ መንግሥት የቁም እስር ላይ ነበሩ።
ይህ ሹመት አዲሱ የሶማሊያ መንግሥት አልሸባብ ላይ የስነ-ልቦና ጦርነት ለማካሄድ ከሚያደርገው ጥረቶች አካል ሳይሆን አይቀርም በማለት የሚያስረዱ ተንታኞች አሉ።
በተቃራኒው ሌሎች ደግሞ ይህ ሹመት አልሸባብ ለፈጸማቸው አሰቃቂ ጥቃቶች እና ወንጀሎችን መዘንጋት ነው ይላሉ።
የቀድሞ የአልሸባብ ቃል አቀባይ በአገሪቱ አዲስ መንግሥት መቋቋሙን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት ከተሰጣቸው 25 ሚኒስትሮች እና 26 ምክትል ሚኒስትሮች መካከል ይገኙበታል።
አዲሱ ካቢኔ በአገሪቱ ምክር ቤት በ229 ድምጽ የጸደቀ ቢሆንም በ7 አባላቱ ተቃውሞ ሲገጥመው አንድ አባል ደግሞ ድምጹን አቅቧል።
የተባበበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶማሊያ ቢሮ በአገሪቱ መረጋጋትን፣ እርቅና ልማትን ለማስፈን ከአዲሱ ካቢኔ ጋር እንደሚሰራ አስታውቋል።
ሮቦው ማን ናቸው?
በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙደ አስተዳደር ውስጥ ሚንስትር ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙት ሮቦው፤ የአልሻባብ ቃል አቀባይ ሆነው አገልግለዋል።
በ2018 በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በቀድሞ አስተዳደር ስር በቁም እስር ላይ ቆይተዋል።
አቡ መንሱር በመባልም የሚታወቁት ሙክታር ሮቦው፤ እአአ ነሐሴ 2017 ለሶማሊያ መንግሥት እጃቸውን ሰጥተው ነበር።
ይህም ከአልሻባብ የከዱ ከፍተኛው አባል አድርጓቸዋል።
በታህሳስ 2018 በሶማሊያ ለደቡብ ምዕራብ ክልል አስተዳዳሪነት የምርጫ ዘመቻ ሲያደርጉ ታስረው ለቁም እስር ተዳርገው ነበር።
በወቅቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስመልክቶ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፤ ሮቦው በባይዶዋ ሚሊሻዎችን ሲያደራጁ ነበር ብሏል።
የወቅቱ የሶማሊያ መንግሥት ሮቦው ከጽንፈኛ አመለካከታቸው አልተላቀቁም የሚል ክስ አቅርቦባቸው ነበር። መታሰራቸውን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ሙክታር ሮቦው የርዕዮተ ዓለም ልዩነትን በመጥቀስ ከአልሻባብ መውጣታቸውን በ2013 አስታውቀዋል።
በኋላም ቡድኑን የሚዋጋ የራሳቸውን ቡድን አቋቁመዋል።
እአአ ሰኔ 2017 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በአልቃይዳ የሰለጠኑትን ታጣቂ ከሽብር መዝገቡ ውስጥ ፍቋል። ያሉበትን ለጠቆመ ሰው ሊሰጥ የነበረውን አምስት ሚሊዮን ዶላርም አንስቷል።












