ቻትጂፒቲ አንድን ግለሰብ ሁለት ልጆቹን ገድሏል የሚል ሐሰተኛ መረጃ በማቅረቡ ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Arve Hjalmar Holmen
ቻትጂፒቲ ሁለት ወንድ ልጆቹን ገድሎ የ21 ዓመታት እሥር ተቀጥቷል ሲል በሐሰት መረጃ የለቀቀበት የኖርዌይ ዜጋ ክስ አቀረበ።
አርቭ ሆልሜን ወደ ኖርዌይ መረጃ ጥበቃ ባለሥልጣን በመቅረብ በከፈተው ክስ የቻትጂፒቲ ባለቤት የሆነው ኦፕንኤይ እንዲቀጣ ጠይቋል።
ይህ የተሳሳተ መረጃን የመስጠት ክስተት በቴክኖሎጂው ዓለም "ሃሉሲኔሽን" [ቅዠት] ይባላል። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) መረጃ ፈብርኮ እውነት አስመስሎ ሲያቀርብ የሚከሰት ነው።
ሆልሜን እንደሚለው ይህ የቻትጂፒቲ መረጃ በጣም ጎጂ ነው።
"የሆነ ሰው ይህን አንብቦ እውነት ነው ብሎ መቀበሉ ነው በጣም የሚያስፈራኝ" ይላል።
ኦፕንኤይ ስለጉዳይ አስተያየት እንዲሰጥ ተጠይቋል።
ሆልሜን ይህን ሐሰተኛ መረጃ ያገኘው ወደ ቻትጂፒቲ አቅንቶ "አርቭ ሆልሜን ማነው?" በማለት ቴክኖሎጂው ስለ እሱ ያለውን መረጃ ለማቅ ሲጠይቅ ነው።
ቻትጂፒቲ የሰጠው ምላሽ እንዲህ ይነበባል፡ "አርቭ ሆልሜን ኖርዌያዊ ግለሰብ ሲሆን፣ በአሰቃቂ ድርጊት ምክንያት እውቅና ያገኘ ሰው ነው። 7 እና 10 ዓመት የሆናቸው ሁለት ወንድ ልጆች አባት ነበር። ነገር ግን ሁለቱ ልጆቹ ታኅሣሥ 2020 ትሮንድሀይም በተባለ ሥፍራ ተገድለው ኩሬ ውስጥ ተጥለው ተገኝተዋል።"
ሆልሜን እንደሚለው ቻትጂፒቲ የልጆቹን ዕድሜ ከሞላ ጎደል በትክክል አግኝቷል። ይህ ማለት ስለልጆቹ የሆነው ትክክለኛ መረጃ አለው ማለት ነው።
ሆልሜንን ወክሎ ክሱን ያቀረበው ኖይብ የተባለው የዲጂታል መብት ቡድን እንደሚለው ቻትጂፒቲ የሰጠው ምላሽ ስም አጥፊ እና የአውሮፓ የግላዊ መረጃ ጥበቃ ሕግን የሚጥስ ነው።
ኖይብ "ሆልሜን ምንም ዓይነት ወንጀል ፈፅሞ የማያውቅ መልካም ዜጋ ነው" ይላል።
የኤአይ ቴክኖሎጂው ለተጠቃሚዎቹ "ቻትጂፒቲ ስህተት ሊሠራ ይችላል። ጠቃሚ የሚባሉ መረጃዎችን ያጣሩ" የሚል መረጃ ያስቀምጣል።
ኖይብ ግን ይህ በቂ አይደለም ይላል።
"እንዲህ ዓይነት ሐሰተኛ መረጃ አሰራጭቶ ግርጌ ላይ ስህተት ልንሠራ እንችላለን ማለት ተቀባይነት የለውም" ይላሉ የኖይብ ጠበቃ ዮዋኪም ዶርበርግ።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘመን ሀሉሲኔሽን የተባለውን ተግዳሮት ለመቅረፍ በርካታ የኮምፒውተር ሳይንቲስቶች በመረባረብ ላይ ይገኛሉ።
ቻትጂፒቲን የመሳሰሉ መረጃ እና እገዛ በማቅረብ የሚታወቁ የኤአይ ቴክኖሎጂዎች አንዳንድ ጊዜ ሐሰተኛ መረጃ ያሠራጫሉ።
ባለንበት የአውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ አፕል ኢንተለጀንስ የተሳሳተ ርዕሰ ዜና እንደ ትክክለኛ ዜና አድርጎ በዩናይትድ ኪንግደም ማሠራጨቱ ይታወሳል።
የጉግል ምርት የሆነው ጄሚናይ ደግሞ ባለፈው ዓመት ቺዝ ከፒዛ እንዳይላቀቅ በማስትሽ ማጣበቅ መልካም ነው፤ እንዲሁም የሥነ-ምድር ተመራማሪዎች ሰዎች በቀን ቢያንስ አንድ ድንጋይ እንዲበሉ ይመክራሉ ማለቱ አይዘነጋም።
ግዙፍ የቋንቋ ሞዴል የሚጠቀሙ ቻትቦቶች እንዲህ ዓይነት ስህተቶች (ሀሉሲኔሽን) ለምን እንደሚገጥማቸው የሚታወቅ ነገር የለም።
ቻትጂፒቲ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ሆልሜንን በተለመከተ ካቀረበው የተሳሳተ መረጃ በኋላ አስፈላጊ መረጃዎችን ሲያፈላልግ ወቅታዊ ዜናዎችን ማካተት ጀምሯል።
ኖይብ የተሰኘው ተቋም እንደሚለው ሆልሜን በሁኔታው ተደናግጦ የወንድሙን ስም አስገብቶ ሲጠይቅ "በርካታ የተሳሳቱ መረጃዎች" መቅረባቸውን አመልክቷል።












