በቴክሳስ አንድ የጭነት መኪና ውስጥ ቢያንስ 40 ሰዎች ሞተው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሳን አንቶኒዮ ቴክሳስ ግዛት ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ አንድ የጭነት መኪና ውስጥ ስደተኞች እንደሆኑ የታመኑ ቢያንስ 46 ሰዎች ሞተው ተገኙ።
በህይወት የተረፉ አራት ህጻናትን ጨምሮ 16 ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን አንድ የእሳት አደጋ ባለስልጣን ተናግረዋል።
በህይወት የተረፉ ሰዎች ሰውነታቸው በሙቀት ግሎ እንደነበርና በከፍተኛ ሁኔታም መዛል ታይቶባቸዋል ተብሏል።
ከአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር 250 ኪሎሜትር ላይ የምትገኘው የሳን አንቶኒዮ ከተማ ለህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ዋና መተላለፊያ ናት።
ወደ አሜሪካ መሻገር የቻሉ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን ለማጓጓዝ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የጭነት መኪኖችን ይጠቀማሉ።
“የሞቱት ሰዎች ቤተሰብ አላቸው። የተሻለ ህይወት ለማግኘትም ይሆናል ወደዚህ የመጡት።አሰቃቂ የሰብአዊ ሁኔታ ነው” በማለት የሳን አንቶኒዮ ከንቲባ ሮን ኒረንበርግ ተናግረዋል።
የሳን አንቶኒዮ የእሳት አደጋ መከላከያ አዛዥ ቻርለስ ሁድ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪዎች መጀመሪያ ወደ ስፍራው የደረሱት በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር 12 ሰዓት ከምሽቱ ነው ።
“የጭነት መኪናውን በር ከፍተን ስናይ እንዲህ የተደራረቡ አስከሬን እናያለን ብለን መቼም አልጠበቅንም። ማናችንም ብንሆን ያንን አስበን ወደ ሥራ አንመጣም" ብለዋል ።
አሽከርካሪ የሌለው የጭነት መኪና ምንም አይነት የአየር ማቀዝቀዣ እንዲሁም ለመጠጥም የሚሆን እንዳልነበረው አክለዋል።
የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርሴሎ ኢብራርድ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት መካከል ሁለት ጓቲማላውያን ይገኙበታል ብለዋል።
የሌሎቹ ተጎጂዎች ዜግነት እስካሁን አልተገለጸም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሶስት ሰዎች በእስር ላይ ሲሆኑ ምርመራውም ለፌደራው ፖሊሶች ተላልፏል።












