ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤድዋርድ ስኖውደን የሩሲያ ዜግነት ተሰጠው
በርካታ የአሜሪካ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ይፋ ያደረገው የቀድሞው የአሜሪካ የደህንነት ሠራተኛ ኤድዋርድ ስኖውደን የሩሲያ ዜግነት ተሰጠው።
ውሳኔው ሰኞ ምሽት በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፊርማ ጸድቋል።
በ2013 በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካዊያን ላይ ተጸዕኖ ያሳረፈውን የአሜሪካ የደህነንት ኤጀንሲ (ኤንኤስኤ) ፕሮግራም ይፋ ያደረገው የ39 ዓመቱ ስኖውደን በስደት ሩሲያ ውስጥ በመኖር ላይ ይገኛል።
አሜሪካ ውስጥ ክስ የተመሠረተበት ስኖውደን በዜግነቱ ጉዳይ እስካሁን በይፋ አስተያየቱን አልሰጠም።
ኤንኤስኤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካዊያንን ስልክ ልውውጥ መጥለፉ በሜሪካ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ህገወጥ ተብሎ በ2020 ውሳኔ ተላልፎበታል።
ከውሳኔው በኋላ ስኖውደን ትክክለኛ ስለመሆኑ እንደተሰማውተናግሯል።
የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት ኤንኤስኤ በይፋ የስልክ ጥሪዎችን ስለመጥለፉ ምንም ባላሉበት ወቅት ነው ስኖውደን ጉዳዩን ይፋ ያደረገው።
ጉዳዩ ይፋ መውጣቱን ተከትሎ ባለስልጣናት ኤንኤስኤ ፕሮግራም የሃገር ውስጥ የሽብርተንነት ሴራን ለመበጣጠስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ሲሉ ተከራክረዋል።
ባሳሊ ሳኢድ ሞአሊን፣ አህመድ ናስር ታሊ ሞሐመድ፣ ሞሐመድ ሞሐሙድ እና ኢሳ ዴሮሄ ተባሉ ግለሰቦች በሶማሊያ ለሚንቀሳቀሰው አል-ሻባብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ያወቅነው በዚህ ፕሮግራም ነው ብለዋል።
የስኖውደን ጠበቃ አናቶሊ ኩቼሬና እንዳሉት ደንበኛቸው በሩሲያ ጦር ውስጥ ባለመሥራቱ ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ፑቲን ያቀረቡት የከፊል ክተት አዋጅ አይመለከተውም።
የሩሲያ ባለስልጣነት በዚህ ክተት ተጨማሪ 300 ሺህ ወታደሮችን እንደሚፈልጉ ያስታወቁ ቢሆንም ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞታል።
በተቃዋሚ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን እንደተዘገበው እስከ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ወደ ጦሩ ሊካተቱ ይችላሉ።