የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ቢሮዎች ከሙስና ምርመራ ጋር በተያያዘ ተበረበሩ

ታትሟል

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አዘጋጇ ኳታር ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ጉቦ ሰጥታለች የሚል ክስ መቅረቡን ተከትሎ ምርመራዎች ተጀመሩ።

በቤልጂየም መዲና የሚገኘው የህብረቱ የብራሰልስ ቢሮዎችም በመርማሪዎች ፍተሻ ተካሂዶባቸዋል።

ፍተሻዎቹ የተጀመሩት አርብ ዕለት ሲሆን ለ20 ያህል ጊዜም መካሄዱ ተገልጿል።

የቤልጂየም ፖሊስ ኳታር ለህብረቱ ባለስልጣት ሰጥታዋለች የተባለውን 1 ሚሊዮን ዩሮ መያዙን ተከትሎም በፓርላማው ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት የሙስና ቅሌቶች አንዱ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ሮቤታ ሜትሶላ “ዴሞክራሲ አደጋ ላይ ነው” ሲሉ የፓርላማ አባላቱን አስጠንቀቀዋል።

ከሙስናው ጋር በተያያዘ የግሪክ ተወካይዋ የህብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢቫ ካይሊን ጨምሮ አራት ግለሰቦችን የቤልጂየም ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏል።

ኳታር ምንም አይነት ጥፋት እንዳልፈጸመች አስታውቃለች።

የህብረቱ የፓርላማ አባላት ከዚህ ሙስና ጋር በተያያዘ ማክሰኞ ለስብሰባ ይቀመጣሉ።

የቤልጂየም ዓቃብያነ ህግ እንዳስታወቁት ወደ 600 ሺህ ዩሮ የሚገመት ገንዘብ በአንድ ተጠርጣሪ ቤት፣ 150 ሺህ ዩሮ በሌላኛው የህብረቱ ፓርላማ አባል አፓርታማ እና በበዙ መቶ ሺዎች የሚገመት ዩሮ በሻንጣ ውሰጥ በብራስልስ ሆቴል ውስጥ ተገኝቷል።

በተጨማሪም የነዚህ ተጠርጣሪ ፓርላማ አባላት ኮምፒውተሮች እና ተንቀሳቃሽ ስልኮች በመርማሪዎች ተወስደዋል።

ከዓርብ ጀምሮ ለምርመራው አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች እንዳይጠፉ ለመከላከል የ10 የፓርላማ አባላት የትኛውንም የኢሜይልና ሌሎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መረጃዎቻቸውን እንዳያዩ ታግደዋል።

በቤልጂየም ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት አራቱ ተጠርጣሪዎች "በወንጀለኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ፣ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና በሙስና ወንጀል" ክስ እንደተመሰረተባቸው አቃቤ ህግ እሁድ እለት በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

ለስምንት ዓመታት የህብረቱ የፓርላማ አባል የሆኑት ኢቫ ካይሊ በፖርላማው ፕሬዚዳንት ሜሶላ ከስራቸው ታግደዋል።

በተጨማሪው ከፓርላማው የሶሻሊስቶች እና ዴሞክራቶች ኮሚቴ እንዲሁም ከግሪክ ፓሶክ ፓርቲም መባረራቸው ተነግሯል።

በግሪክ የሚገኙ አቃብያነ ህግ የኢቫ ካይሊ ንብረቶችን በሙሉ ማገዱ ተዘግቧል።

ኳታር የአውሮፓ ህብረት አባላትን ድጋፍ ለማግኘት ለባለስልጣናቱ ጉቦ ሰጥታለች በሚል ክስ ላይ በተደረገው ምርመራ ስድስት ሰዎች አርብ እለት በቁጥጥር ስር ውለው ነበር። በኋላ ሁለቱ ተፈተዋል።

ተጠርጣሪዎች እስካሁን እነማን እንደሆኑ የአውሮፓ ህብረት በይፋ ባያሳውቅም ኢቫ ካይሊ ከተከሰሱት መካከል መሆናቸው ታውቋል።