ተመሳሳይ መንትዮች የሚጋሯቸው ያልተጠበቁ ማንነቶች እና ባህሪያት

ሁለት ተመሳሳይ መንትዮች ሰልፊ እየተነሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

መንትያ ካልዎት ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል አንዱን ተጠይቀው ይሆናል።

"እሱ የሆነውን ነገር ሳይነግርህ የማወቅ አቅም አለህ?"

"አንዳችሁ ሌላኛው ሲታመም ታውቃላችሁ?"

"አንዳችሁ ሌላኛችሁን መስላችሁ ተገኝታችሁ ታውቃላችሁ?"

የሁለት የተለያዩ ግለሰቦች ቀልብ እና ቁመና ለጥንት አፈ ታሪኮች፣ ለሙዚቃ፣ ለፊልሞች እና ለልብ ወለዶች መነሻ በመሆን አገልግሏል።

ነገር ግን ለጥበብ ሰዎች ብቻ ሳይሆን መንትዮች የሳይንስ ተመራማሪዎችንም ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ ይስባሉ።

የእኛ ዘረመል እና አካባቢ እንዴት በባህሪያችን እና ማንነታችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ለማጥናት ልዩ ዕድል ይሰጣሉ።

እኛን እኛ ያደረገን ተፈጥሮ ነው ወይስ አስተዳደግ ለሚለውም ምላሽ ይኖራቸው ይሆናል።

የአምስት ቀን ሕፃን ልጆች ብርድ ልብስ ላይ ተኝተው
የምስሉ መግለጫ, ተመሳሳይ መንትዮች ሁሉንም ዘረመሎቻቸውን በሚባል መልኩ የሚጋሩ ሲሆን በጣም ተመሳሳይም ናቸው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁለት ዓይነት መንትዮች አሉ።

የማይመሳሰሉ መንትያዎች (fraternal twins) በአንድ ጊዜ ከተለቀቁ እና ከተለያየ የወንዴ ዘር ከዳበሩ ሁለት የተለያዩ እንቁላሎች የሚገኙ ናቸው።

ልክ እንደ መደበኛ እህትማማቾች እና ወንድማማቾች በአማካይ ግማሽ ያህሉን ዘረመላቸውን ይጋራሉ።

ተመሳሳይ መንትዮች የሚፈጠሩት ደግሞ አንድ የወንዴ ዘር እና የዳበረ እንቁላል ወደ ሁለት ጽንሶች ሲከፈል ሲሆን በዚህም የተነሳ ሁሉንም ዘረመሎች የሚጋሩ እና ብዙውን ጊዜ በጣም ተመሳሳይ ናቸው።

በጣም ጥቂት ከመሆናቸው የተነሳ ከ1,000 ከሚወለዱ ሕፃናት ውስጥ በግምት በሦስቱ ብቻ ይከሰታል።

ራሷ መንትያ ወንድም ያላት ፕሮፌሰር ናንሲ ሴጋል በሥራ ዘመኗ በሙሉ ይህንን ስታጠና አሳልፋለች።

በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የመንትዮች ጥናት ማዕከልን የምትመራ ሲሆን የዘረመል እና የሥነልቡና ተመራማሪ ነች።

ፕሮፌሰር ሴጋል "መንትዮች የየትኛውንም ባህሪ ዘረመል እና የአካባቢ ተጽዕኖዎች፣ ከእውቀት እስከ በፍጥነት እስከ መሮጥ፣ከሰብዕና እስከ ቁመት እና ክብደት እንድንመለከት ያስችሉናል" ብላለች።

የተለመደው የመንትዮች ምርምር በዘረመል ተመሳሳይ መንትዮችን ከማይመሳሰሉ መንትዮች ጋር ያወዳድራል።

ተመሳሳይ መንትዮች በአንድ የተወሰነ ባህሪ ላይ የበለጠ ተመሳሳይ ከሆኑ ይህ የሚያሳየው ዘረመሎች በባህሪ እድገት ውስጥ የተወሰነ ሚና እንደሚጫወቱ ነው።

ዘረመሎች ቁመታችንን፣ክብደታችንን እና የማሰብ ችሎታችንን በመቅረጽ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ምንም አያስደንቅ ይሆናል።

ነገር ግን የመንትዮች ጥናት ዘረመሎችን በአንዳንድ በጣም ግላዊ ባህሪዎቻችን እና ብቃቶቻችን ውስጥ ሚና እንደሚጫወቱ አረጋግጠዋል።

ፕሮፌሰር ሴጋል እንዳሉት "መንትዮች… በጣም ብዙ የተለያዩ ባህሪያትን ለማጥናት ጥቅም ላይ ውለዋል። ሃይማኖታዊነት እና ማኅበራዊ አመለካከቶች፣ የሞት ቅጣት፣ የአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀም [እና] መዋዕለ ንዋይን ፈሰስ ስለማድረግ ተጠንተዋል።"

ለምሳሌ በአሜሪካ፣በኔዘርላንድስ እና በአውስትራሊያ የተደረጉ ጥናቶች ተመሳሳይ መንትዮች፣ ተመሳሳይ ካልሆኑ መንትዮች፣ በተለይ በጉልምስና ዕድሜ ላይ፣ ለሃይማኖት ተመሳሳይ አመለካከት የመጋራት ዕድላቸው ሰፊ ነው።ይህ የሚጠቁመው ዘረ መላቸው በእምነት ውስጥ ሚና እንደሚጫወቱ ነው።

ፕሮፌሰር ሴጋል እንዳሉት የእኛ ዘረመሎች በእግዚአብሔር እንድናምን የሚወስኑ ሳይሆኑ እንደ ብልህነት ወይም ስሜታዊነት ባሉ ውስብስብ ባህሪያት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ በመሆናቸው የበለጠ እንድንሰራ ያደርገናል።

 ሮዝ ጃኬት የለበሰች ሴት በሁለት አረጋውያን ሴቶች መካከል ቆማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኤልዛቤጥ ሃሜል (በስተግራ) እና አን ሀንት (በስተቀኝ) ከመገናኘታቸው በፊት ለ78 ዓመታት ተለያይተው ነበር። ፕሮፌሰር ናንሲ ሴጋል (መሃል) እነዚህ እህትማማቾች ላይ ሰፊ ጥናት እና ምርመር አካሂዳለች

ተለያይተው ያደጉ መንትዮች

በፕ/ር ሴጋል ጥናት እጅግ አስደናቂው ግኝት አብረው ያላደጉ ተመሳሳይ መንትዮችን በማጥናት የተገኘ ነው።

"የመጀመርያው በሰብዕና ላይ ነው።ይህ የሚያስደንቀው ምንድን ነው በሀይለኝነት እና ባህላዊ መሆን ውስጥ ... በአንድ ላይም ሆነ እና ተለያይተው ባደጉ ተመሳሳይ መንትዮች መካከል ልዩነት የላቸውም። ይህ የሚነግረን ምንድን ነው ዘመዳማቾች ሆነው አብረው የሚኖሩ ሰዎች፣ መመሳሰላቸው የመጣው ከሚጋሩት ከባቢ ሳይሆን ዘረ መላቸው ካለው ተፅዕኖ ነው።"

በፕሮፌሰር ሴጋል ጥናት ከተሳተፉት መንትዮች መካከል እንደተወለዱ ተለያይተው ያደጉት መንትዮቹ አን ሀንት እና ኤልዛቤጥ ሃሜል ይገኙበታል።

መንትዮቹ ለ78 ዓመታት ተለያይተው በማደግ የዓለም ክብረ ወሰንን ጨብጠዋል።

በአሜሪካ በድጋሚ የተገናኙት አን እንግሊዝ ውስጥ ተወልዳ ካደገች እና ከኖረች በኋላ እህቷን ኤልሳቤጥን መፈለግ ከጀመረች በኋላ ነው።

የዚህ ጥናት ውጤት አን እና ኤልዛቤጥ በርካታ የባህርይ መመሳሰሎች እንዳሏቸው ያሳየ ሲሆን እና ሁለቱም ያገቧቸው ወንዶች ጂም ይባላሉ።

በሌሎች ጥናቶች የተገኙት አንዳንድ ተመሳሳይነቶች የበለጠ እንግዳ ናቸው።

"ያልተለመዱ ጠባዮች እና ባህሪያት እንኳን ተወራርሰዋል።ለምሳሌ አንድ ተመሳሳይ መንትዮች ሁለቱም የስዊድን ብራንድ ያለውን የጥርስ ሳሙናን ይጠቀማሉ። ሌላ ተመሳሳይ መንትዮች በሚኒሶታ አየር ማረፊያ ሲገናኙ ሁለቱም ሰባት ቀለበቶች፣ሦስት አምባሮች እና የእጅ ሰዓት አድርገው ነበር።"

የመንትዮቹ የጋራ ባህሪያቱ በዚህ ብቻ አላበቃም።

ፕሮፌሰር ሴጋል "ሌላ ተመሳሳይ መንትዮች ደግሞ እጃቸው ላይ የሚያጠልቁት ጌጣ ጌጥ፣ ወደ ንጽህና ቤት ከመሄዳቸው በፊት እና በኋላ ያላቸው እጅ የመታጠብ ልምድ ተመሳሳይ ነበር። ምናልባት ለጀርሞች በጣም የተጋለጡ እና በንጽህና ላይ ስሱ ሆነው ይሆናል" ብላለች።

ተለያይተው ያደጉ ስኮትላንዳውያን ተመሳሳይ መንትዮች ደግሞ የተጠበሰ ዳቧቸውን አራት ቦታ ከቆረጡ በኋላ ሦስቱን ብቻ ይመገባሉ። ይህ የምግብ ፍላጎታቸውን የመከታተል ፍላጎትን ይጠቁማል፤ ወይም ሁሉንም ሰሃናቸው ላይ ያለውን ነገር ላለመብላት መፈለጋቸውን ስትል ታክላለች።

"እነዚህ ነገሮች . . . አጋጣሚዎች በድንገት እንደማይመጡ ይጠቁማሉ። ሁላችንም ያልተለመዱ እና ግራ የሆኑ ልማዶች አሉን።እነዚያ ደግሞ ከየትኛውም ቦታ አይመጡም።በተወሰነ ደረጃ ማንነታችንን ያሳያሉ።" ትላለች ፕሮፌሰር ሴጋል።

በተመሳሳይ ስም የሚጠሩት መንትዮች

እጅግ አስገራሚው የተመሳሳይ መንታዎች ጉዳይ በአሜሪካ ከሚኒሶታ የተገኙት ናቸው። ሁለቱም ስማቸው ጂም ይባላል።

በተወለዱበት ጊዜ ተለያይተው በ 39 ዓመታቸው እንደገና ለመገናኘት በቅተዋል። ሕይወታቸው እጅጉን ተመሳሳይ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደባቸውም።

ሁለቱም ሊንዳ የምትባል ሴት አግብተው ከፈቱ በኋላ ቤቲ የምትባል ሴት እንደገና አግብተዋል።

ሁለቱም ቶይ የሚባል ውሻ እና ጄምስ አላን የሚባል ልጅ ነበራቸው። ሁለቱም ጥፍራቸውን የመብላት ልምድ፣ በአንድ ባህር ዳርቻ ለእረፍ ት የመንሸራሸር ዝንባሌ አላቸው።

መንትዮቹ የሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ቶማስ ቡቻርድ ባደረጉት ጥናት ላይ ተሳትፈዋል።

ምንም እንኳን ተለያይተው ቢያድጉም በሚያስደንቅ ሁኔታ ተመሳሳይ ባህሪ፣ ፍላጎት ዝንባሌ እንዳላቸው ማወቅ ተችሏል።

እነዚህ የሚገርሙ ምሳሌዎች ጥያቄ ያጭራሉ፤ እኛ ማሰብ የምንፈልገውን ያህል በምርጫችን እና በባህሪያችን ላይ ብዙ ሥልጣን አለን?

"አንድ ነገር የዘረመል ተጽዕኖ ስላለው ብቻ ሥልጣኑ የለዎትም ማለት አይደለም" ትላለች ፕሮፌሰር ሴጋል። በበርካታ የሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚከሰተውን ፍቺን እንደ ምሳሌ ጠቅሳ፣ በዘረ መል ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ያልተወሰነ የሕይወት ክስተት መሆኑን ታስረዳለች።

ስለዚህ ዘረ መል በዚህ ውስጥ ምን የተለየ ድርሻ ይጫወታል?

"ምናልባት አስቸጋሪ የሆኑ ሰብዕናዎች፤ግትርነት [እና] እንደዚያ ያሉ ባህሪያት። ነገር ግን የእርስዎ ዘረመል ፍቺ አይልም! ለመፋታት ውሳኔ ትወስናላችሁ። ስለዚህ ያ ነፃ ምርጫ በምንም መልኩ በዚህ የተደናቀፈ አይመስለኝም። "

ዋናው ነገር ፕሮፌሰር ሴጋል እንደምትለው ሁል ነገር ፍጹም ነው ብሎ ማሰብ አያስፈልግም። ሰብዕናችንን እና ባህሪያችንን በተመለከተ እኛን ዛሬ ወደሆንነው ማንነት እንድንሆን አድርጎ የወሰደን ምንም አይነት ትክክለኛ ምንጭ የለም።

"ሰዎች አካባቢ ሙሉ በሙሉ እንደቀረፀን ማሰብ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ያ የተሳሳተ ግንዛቤ ይመስለኛል" ብለዋል ፕሮፌሰር ሴጋል።