ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጋዛ የተኩስ አቁም ድርድር ችላ እንዳይባል ባይደን አሳሰቡ
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ወገኖች ችላ እንዳይሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስጠነቀቁ።
ባይደን ለተኩስ አቁም “ከመቼውም በላይ ቅርብ ነን” ቢሉም ሐማስ ግን እርግጠኛ አለመሆኑን ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ወደ እስራኤል ሄደው ስምምነቱ እንዲደረስ እንደሚገፋፉ ተገልጿል።
አሜሪካ፣ ኳታር እና ግብፅ የተኩስ አቁም የሚደረግበትና ታጋቾች የሚለቀቁበት ስምምነት ያረቀቁ ሲሆን ይህም በእስራኤልና ሐማስ መካከል ያለውን ክፍተት ያጠበዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ጦርነቱ ቀጠናዊ መልክ ሊይዝ ይችላል በሚለው ስጋት ውስጥ ከኳታር አንዳች ተስፋ ይጠበቃል።
ላለፉት ሁለት ቀናት የተደረገው ድርድር “ገንቢና በአዎንታዊ መንፈስ የተከናወነ” ነው ሲሉ አደራዳሪዎች ገልጸዋል።
በቀጣይ ቀናትም ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ካይሮ ተገናኝተው እንዴት ሐሳቡ እንደሚተገበር ውይይቶች ይጠበቃሉ። በዶሃ የቀረቡ ረቂቅ ሐሳቦች ተቀባይነት ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከኳታርና ግብፅ አመራሮች ጋር የተነጋገሩት ባይደን “ከፍተኛ ድጋፍ” ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
ብሊንከንን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የላኩት “ለእስራኤል ደኅንነት መጠበቅ ያለኝን ቁርጠኛነት ለማሳየት” ነው ያሉት ባይደን፣ “የተኩስ አቁም ተደርጎ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚደረገውን ጥረት ማንም በቀጠናው ያለ አካል ችላ ማለት የለበትም” ሲሉ አሳስበዋል።
አደራዳሪዎቹ የሰጡት መግለጫ ተስፋ ቢሰጥም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ብዙ ርቀት መጓዝ ያስፈልጋል።
ከዚህ ቀደምም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የተኩስ አቁም ስምምነት ከጫፍ ደርሷል ቢሉም ብዙም በሐሳቡ የተስማማ አልተገኘም።
በድርድሩ ላይ ባይሳተፉም ከኳታርና ግብፅ ጋር ንግግር ያደረጉ የሐማስ ከፍተኛ አመራር ለቢቢሲ “የንቅናቄው አመራር የደረሰው መረጃ በዶሃ በተደረገው የተኩስ አቁም ውይይት ላይ የተላለፈው ውሳኔ ሐምሌ 2 ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ነጥቦች እንደማይተገበሩ ነው” ብለዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ሐማስ ታጋቾችን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆኑን እንዲቀይር የሚያደርግ ጥረትን እደግፋለሁ” ማለታቸውን ቢሯቸው ያወጣው መግለጫ ይጠቅሳል።
በሐማስ ጥቃት 1,200 ሰዎች ሲገደሉ፣ 251 ሰዎች ታግተዋል። በእስራኤል ጥቃት በጋዛ ከ40,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ኅዳር ላይ በተደረሰ የተኩስ አቁም 105 ታጋቾች ከጋዛ ሲለቀቁ፣ 240 ፍልስጤማውያን እስረኞች ከእስራኤል ተለቀዋል።
የመጀመሪያው የስምምነት አካል የተረቀቀው በባይን ሲሆን፣ግንቦት 27 በእስራኤል የቀረበው ረቂቅ ለስድስት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁምና የእስራኤል ወታደሮች በሕዝብ ከተጨናነቁ የጋዛ አካባቢዎች እንዲወጡ ይላል።
በእስራኤል የታሰሩ ፍልስጤማውያን ተለቀው በምላሹ ሴቶችና አዛውንቶች ታጋቾች እንዲለቀቁም ረቂቁ ላይ ሐሳብ ቀርቧል።
በሁለተኛው ዙር በዘላቂነት ተኩስ አቁም ተደርጎ ሁሉም ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን በሦስተኛው ዙር ጋዛን መልሶ መገንባት ተካቷል።
ሆኖም እስራኤል በጋዛ የምታደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። ከካሀን ዩኑስና ዴር ባላህ ነዋሪዎች እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። ይህም ሰብአዊ ስፍራዎችን እያጠበበ ይሄዳል።
በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤማውያን ስደተኞች ኤጀንሲ “ቤተሰቦች የሚሸሹበት ስለሌላቸው ፈርተዋል። ሞትና ውድመት ያንዣበበበት ጨለማ ውስጥ መኖር ቀጥለዋል” ብሏል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ ሰብአዊ ብላ በከለለቻቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በተጠለሉባቸው አካባቢዎች ፖሊዮ እየተሰራጨ መሆኑ የተኩስ አቁምን ከምን ጊዜውም በላይ አስፈላጊ ያደርገዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዩ ጉተሬዝ “ግልጽ እንሁን። ፖሊዮን ለማጥፋት ሰላምና አፋጣኝ ተኩስ አቁም ያሻል” ብለዋል።