እውቁ አፍጋናዊ የሃይማኖት መሪ ሰው ሰራሽ እግር ውስጥ በተደበቀ ቦምብ ተገደሉ

ታሊባንን እና የሴቶችን የመማር መብት በመደገፍ የሚታወቁት እውቁ የሃይማኖት መሪ በአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ተገደሉ።
ሼክ ራሂሙላህ ሃቃኒ የተገደሉት አንድ አጥፍቶ ጠፊ በሰው ሰራሽ እግሩ ውስጥ የደበቀውን ቦምብ ካፈነዳ በኋላ መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።
ለሼክ ሃቃኒ ግድያ እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን ባይኖርም፤ ከዚህ ቀደም ግን ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) በሃይማኖት መሪው ላይ የግድያ ሙከራዎችን አድርጎ ነበር።
ዘገባዎቹ እንደጠቆሙት ከሆነ የአጥፍቶ መጥፋቱ ጥቃት የተፈጸመ በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል ውስጥ ነው።
ሼክ ሃቃኒ የታሊባን መንግሥት ደጋፊ የነበሩ ሲሆን፣ የኢስላሚክ ስቴት አንድ ክንፍ የሆነውን የኮህራሳን ግዛት ቡድንን ደግሞ አጥብቀው በመተች ይታወቃሉ።
ይህ የኢስላሚክ ስቴት አጋር የሆነው ቡድን የታሊባን አስተዳደርን የሚቃወም ሲሆን፣ በአፍጋኒስታን በስፋት ይንቀሳቀሳል።
ሼክ ሃቃኒ ታሊባን አፍጋኒስታንን መልሶ በመቆጣጠር ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ፣ በአገሪቱ በአጥፍቶ ጠፊ የተገደሉ ትልቅ ስም ያላቸው ግለሰብ ሆነዋል።
“ለእስላማዊ ኤሚሬት አፍጋኒስታን ይህ ትልቅ ኪሳራ ነው” ሲሉ አንድ የታሊባን ከፍተኛ አመራር ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ ከዚህ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ጀርባ ማን እንዳለ ለማወቅ ምርመራዎች ተጀምረዋል ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
የሴቶች የመማራ መብት አከራካሪ በሆነባት በአፍጋኒስታን፤ ሼክ ሃቃኒ ከዚህ ቀደም የአፍጋኒስታን ሴቶች ትምህር ቤት መሄድ ሊፈቀድላቸው ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ሼክ ሃቃኒ ከወራት በፊት ለቢቢሲ ቃለ ምልልስ በሰጡበት ወቅት፤ “በሸሪአ የሴቶች ትምህርት አልተከለከለም። ምንም ማሳመኛ የለም” ሲሉ ተናግረው ነበር።
“ሁሉም መጽሐፍት የሴቶች ትምህርት የተፈቀደ እና ግዴታ እንደሆነ ያትታሉ፤ ለምሳሌ እስላማዊ በሆኑ እንደ ፓኪስታን እና አፍጋኒስታን ባሉ አገራት አንድ ሴት ብትታመም እና ሕክምና ቢያስፈልጋት ሴት ዶክተር ብታክማት የበለጠ ተመራጭ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።
ታሊባን አፍጋኒስታንን ተቆጣጥሮ ከያዘ በኋላ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የሴቶች ሁለተኛ ድረጃ ትምህር ቤቶች እንዲዘጉ አድርጓል።
ሼክ ሃቃኒ ከዚህ ቀደም ከሁለት የግድያ ሙከራዎች አምልጠዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ እአአ 2020 ላይ አይኤስ በፓኪስታኗ ፔሽዋራ ከተማ የሃይማኖት ትምህር ቤት ላይ የፈጸመው ጥቃት ይገኝበታል። በዚህ ጥቃት ቢያንስ 7 ሰዎች ተገድለዋል።












