በጋዛ ከተማ በሐማስ ኃይሎች እና በጎሳ ታጣቂዎች መካከል በተነሳ ግጭት ነዋሪዎች ተገደሉ

የፖሊስ ደንብ ልብስ የለበሰ እና የታጠቀ ግለሰብ መንገድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ጋዛ ከተማ ውስጥ በሐማስ የጸጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ የዶሙሽ ቤተሰብ አባላት መካከል በተነሳ ግጭት ቢያስን 27 ሰዎች ተገደሉ።

የዓይን እማኞች እደተናገሩት ጭንብል የለበሱ የሐማስ ታጣቂዎች እና የጎሳ ተዋጊዎች በከተማዋ በሚገኘው የጆርዳን ሆስፒታል አቅራቢያ የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል።

የሐማስ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኙ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን፤ የጸጥታ ኃይሎች ከበባ እንደፈጸሙ እና ታጣቂዎቹን ለመያዝ ከፍተኛ ውጊያ እንዳደረጉ ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ "ሚሊሻዎች [በፈጸሙት] በትጥቅ የታገዘ ጥቃት" ምክንያት ስምንት የሐማስ ተዋጊዎች ተገድለዋል።

የሕክምና ምንጮች በበኩላቸው ቅዳሜ ዕለት ግጭት ከተነሳ ወዲህ 19 የዶሙሽ ጎሳ አባላት እና 8 የሐማስ ተዋጊዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

የዓይን እማኞች እንደሚናገሩት በጋዛ ከተማ ቴል አል ሃዋ በተባለው አካባቢ ግጭት የተነሳው 300 የሚሆኑ የሐማስ ተዋጊዎች የዳሙሽ ታጣቂዎች ወደ ሰፈሩበት የመኖሪያ ሰፈር በኃይል ከገቡ በኋላ ነው።

በሁለቱ ታጣቂዎች መካከል የተነሳው ግጭት በበርካታ ቤተሰቦች ላይ መደናገጥ የፈጠረ ሲሆን ነዋሪዎች በጥይት እሩምታ ውስጥ አካበቢውን ለቅቀው ሄደዋል። ከእነዚህ ነዋሪዎች ውስጥ ብዙዎቹ በጋዛ ጦርነት ወቅት በተደጋጋሚ የተፈናቀሉ ናቸው።

አንድ ነዋሪ፤ "በአሁኑ ጊዜ ሰዎች እየሸሹ የነበሩት የእስራኤልን ጥቃት አልነበረም። እየሸሹ የነበረው ከራሳቸው ሰዎች ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጋዛ ውስጥ ከሚገኙ ታዋቂ ጎሳዎች አንዱ የሆነው የዶሙሽ ቤተሰብ ከሐማስ ጋር ያለው ግንኙነት በውጥረት የተሞላ ነው። ከዚህ ቀደምም የታጠቁ የቤተሰቡ አባላት በተለያዩ ጊዜያት ከሀማስ ጋር ግጭት ውስጥ ሲገቡ ቆይተዋል።

የሐማስ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው ስርዓትን ለመመለስ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጿል። "ከትግሉ ማዕቀፍ ውጪ ያለ ማንኛውን የትጥቅ እንቅስቃሴ" ከባድ እርምጃ እንደሚወሰድበትን አስጠንቅቋል።

ለአሁኑ ግጭት መቀስቀስ አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ አድርገዋል።

ሐማስ፤ የዶሙሽ ታጣቂዎች ሁለት ተዋጊዎቹን ገድለው አምስቱን እንዳቆሰሉ ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር። በዚህም የተነሳ በታጣቂዎቹ ላይ ዘመቻ መክፈቱን ገልጿል።

የዶሙሽ ቤተሰብ ምንጮች በበኩላቸው የሀማስ ኃይሎች የጆርዳን ሆስፒታል ሆኖ ሲያገለግል ወደነበረው ሕንጻ እንደመጡ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል። አል ሳብራ በተባለው አካበቢ የነበሩት ቤቶቻቸው በእስራኤል ጥቃት የወደሙባቸው የቤተሰቡ አባላት በዚህ ሕንጻ ውስጥ ተጠልለው ነበር።

የቤተሰቡ ምንጭ እንደሚናገሩት ሐማስ የዶሙሽ አባላትን ከሕንጻው ማስወጣት የፈለገው በስፍራው ለተዋጊዎቹ አዲስ የጦር ሰፈር ለማቋቋም ነው።

በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ መሠረት፤ ሐማስ የእስራኤል ወታደሮች በቅርቡ ጥለውት የወጡትን የጋዛ አካባቢ ለመቆጣጠር በሚል ለ7,000 የጸጥታ ኃይሎች ጥሪ አድርጓል።

የሲቪል ልብስ የለበሱ እንዲሁም ሰማያዊ የጋዛ ፖሊስ የደንብ ልብስ ያደረጉ የሀማስ የጸጥታ ኃይሎች በተለያዩ ቀጠናዎች መሰማራታቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ። የሐማስ የመገናኛ ብዙኃን ቢሮ ግን "ተዋጊዎችን ጎዳናዎች ላይ" አሰማርቷል መባሉን አስተባብሏል።