ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሻይን ለማጣፈጥ ‘ጨው ጣል አድርጉበት’ የሚለው የባለሙያ ምክር በአሜሪካ እና በዩኬ የፈጠረው ውዝግብ
የአሜሪካዊቷ ሳይንቲስት ሻይ እንዲጣፍጥ ውስጡ ጨው ጣል ማድረግ ጥሩ እንደሆነ ጥናት እና ሙከራዋን መሠረት አድርጋ መክራለች።
ብዙዎች ሐሳቡ ላይዋጥላቸው ይችላል። ሳይንቲስቷ ግን ጨው የገባበት ሻይ ጥዑም ነው ብላለች።
ይህን ጥናት ያካሄደችው ፕሮፌሰር ሚኬሊ ፍራንሲል ናት።
ሻይ ባህላዊ መጠጣቸው የሆነው የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ሕዝብ በጥናቱ ደስተኛ አልሆነም።
በአሜሪካ የዩኬ ኤምባሲ ጣልቃ ለመግባትም ተደገዷል።
“ውድ የዩኬ ሕዝብ ሻይ ውስጥ ጨው መጨመር የአሜሪካ ብሔራዊ ሕግ አልሆነም። ለወደፊትም አይሆንም” ሲል ኤምባሲው ለዩኬ ሕዝብ መልዕክት አስተላልፏል።
በቀን ከ100 በላይ ሲኒ ሻይ በሚጠጣባት በዩኬ እና በአሜሪካ መካከል ሻይ ውዝግብ ሲያስነሳ የመጀመሪያው አይደለም።
እአአ በ1773 በቦስተን እና በቅኝ ግዛት ሥር በነበረው ማሳቹሴትስ በተደረገ ተቃውሞ ላይ የእንግሊዝን ግብር በመቃወም 300 የሻይ የያዙ ሳጥኖች ወደ ባሕር ተጥሏል። ይህም የአሜሪካን አብዮት ያስነሳ ቁልፍ ተቃውሞ ነበር።
ሻይ ውስጥ ጨው ይጨመር ያለችው ተመራማሪ “እኔ የዲፕሎማሲ ግብግብ መፍጠር አልፈልግም” ብላለች።
በፔንስልቬንያ፣ ብራየን ማውር ኮሌጅ ነው የምታስተምረው።
“በጣም ብዙ ኢሜል ነው የደረሰኝ። ጠዋት ስነሳ ይሄ ሁሉ ሰው ሻይ ውስጥ ጨው ስለመጨመር ያወራል ብዬ አልገመትኩም” ብላለች።
ሻይ ውስጥ ለምን ጨው ይጨመራል?
ሐሳቡ አዲስ አይደም። በ18ኛው ከፍለ ዘመን የቻይና ጽሑፎች ላይ ሰፍሯል።
ፕሮፌሰሯ እንደምትለው ጨው ለሻይ ጣዕም ይሰጣል።
በዚህ ዘመን አቀማመም ስለተሻሻለ የጥንቱን ሐሳብ በተሻለ መተግበር ይቻላል።
ተመራማሪዋ እንደምትለው፣ ሻይን መራራ የሚያደርገውን ንጥረ ነገር ጨው ማሸነፍ ይችላል። በተለይ ደግሞ ሲፈላ።
በጣም ትንሽ ጨው ሻይ ውስጥ ሲጨመር መራራውን ጣዕም ያስወግዳል።
“ስኳር እንደመጨመር አይደለም። ሰዎች ሻዩ ጨው ጨው ይለናል ብለው የሰጉ ይመስለኛል” ትላለች።
‘ዘ ኬምስትሪ ኦፍ ቲ’ በተባለው መጽሐፏም ይህንን ታስረዳለች።
“መሞከር ሁሌም መልካም ነው። ሁላችንም ጓዳችን ውስጥ መሞከር እንችላለን። እኔም እሞክራለሁ” ብላለች።
እናቷ ሻይ በ10 ዓመቷ ካፈላችላት ወዲህ ሻይ ትወዳለች።
ቆንጆ ሻይ እንዴት ይፈላል? ለሚለው ሁሉም የየራሱ ምልከታ አለው።
ፕሮፌሰሯ ግን ብትን ሻይ ቅጠል መጠቀምን ትመክራለች።
ሻይ በደንብ ሲማሰል ከውሃ እና ከወተት ጋር መዋሀድም ይችላል።
በስሱ ሎሚ ጠብ ማድረግም ሻይ ያጣፍጣል።
ሻይ ቶሎ እንዳይቀዘቅዝ በአነስተኛ ሲኒ ማቅረብምን ስትመክር፤ ለሻይ የሚሆን ውሃን በማይክሮዌቭ ማሞቅን አጥብቃ ትቃወማለች።
“ጤናማ አይደለም። አይጣፍጥም። ሻይ ቅጠሉ ተሰብስቦ ነው የሚጠብቃችሁ” ስትል ነው የምትገልጸው።
አሜሪካ ውስጥ ጥሩ ሻይ ብዙም እንደማይገኝ ትገልጻለች። “አየርላንድ አገልግሎት መስጫ ጣቢያ የጠጣሁትን ሻይ አሜሪካ ቅንጡ ሆቴል ውስጥ አላገኘውም” ትላለች።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ግን ሁሌም ቆንጆ ሻይ እንደምትጠጣ ትገልጻለች።
“ልክ ዩኬ ስገባ ምርጥ ሻይ እንደምጠጣ አስባለሁ።”
የአሜሪካ ኤምባሲ የፕሮፌሰሯን ሐሳብ ከመቀበል ይለቅ እንደተለመደው ሻይ በማይክሮዌቭ ማፍላትን እንደሚመርጥ ገልጿል።
የዩኬ ካቢኔ ደግሞ ሻይን በሻይ ማንቆርቆሪያ ብቻ በማፍላት እንደሚቀጥል አስታውቋል።