የትራምፕ አስተዳደር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርን የተመለከቱ ሰነዶችን ይፋ አደረገ

ማርቲን ሉተር ኪንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማርቲን ሉተር ኪንግ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኤፍቢአይ በመብት ታጋዩ ላይ ሲያደርጋቸው የነበሩ ክትትሎችን የሚያሳዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ጨምሮ በማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ግድያ ላይ በርካታ መረጃዎችን ይፋ አድርጓል።

በፍርድ ቤት በተላለፈ ትዕዛዝ መሠረት 230 ሺህ ገጾች ያሉትን ሰነድ ከ1977 ጀምሮ ለሕዝብ እንዳይታዩ ታግዶ ቆይቷል።

ታዋቂ የማርቲን ቤተሰብ አባላት የሰነዶቹን ይፋ መደረግን ተቃውመዋል። የሁለቱ በሕይወት ያሉ ልጆቹ የሰጡት መግለጫ "እነዚህን ሰነዶች አላግባብ በመጠቀም የአባታችንን ስም ለመናድ የሚደረገውን ጥረት ሁሉ" አውግዘዋል።

የባፕቲስት የቤተክርስቲያን አገልጋይ የነበረው ኪንግ፣ በሜምፊስ እአአ በሚያዚያ 4/1968 በ39 ዓመቱ በጥይት ተመትቶ ነበር የተገደለው። ቅጥረኛ ገዳይ የሆነው ጀምስ ኧርል ሬይ ግድያውን መፈጸሙን አምኖ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ክዷል።

የኪንግ ጁኒየር ሁለቱ በሕይወት ያሉ ልጆች ማርቲን ሳልሳዊ እና በርኒስ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ "እነዚህን ሰነዶች የሚለቁ ሰዎች በርህራሄ፣ በገደብ እና ለቤተሰባችን ቀጣይ ሐዘን በማክበር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። የእነዚህ ፋይሎች መለቀቅ በሙሉ ታሪካዊ አውዳቸው ውስጥ መታየት አለባቸው። አባታችን በሕይወት በነበረበት ጊዜ፣ በጄ ኤድጋር ሁቨር በፌደራል የምርመራ ቢሮ በኩል በተቀነባበረ ወራሪ፣ አዳኝ እና በጣም አሳሳቢ የሆነ የሐሰት መረጃ እና የክትትል ዘመቻ ያለመታከት ኢላማ ተደርጎበታል" ብዋል።

መግለጫው የመንግሥት ክትትል ኪንግን "የግል ዜጎችን ክብር እና ነፃነት ከልክሏል" ብሏል።

ቤተሰቡ በ1999 በተሳሳተ የሞት ፍርድ የፍትሐ ብሔር ክስ የሲቪል መብቶች መሪው በአንድ ተራ ዘረኛ ግለሰብ የተገደለ ሳይሆን የሰፊ ሴራ ሰለባ ነው የሚለውን የዳኞችን ብይን ጠቅሷል።

በጥር ወር ትራምፕ በኪንግ እና ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ ጋር የተያያዙ ሰነዶች ከሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ግድያ መዛግብት ጋር አንድ ላይ ይፋ እንዲደረጉ አዝዘዋል።

የብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ሰኞ ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የማርቲን ሉተር ኪንግ ሰነዶች እስከ ዛሬ ድረስ በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ለብዙ አሥርት ዓመታት አቧራ ለብሰው ነበር ብለዋል ።

ማርቲን ሉተር ኪንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኪንግ "ህልም አለኝ" በማለት ዋሽንግተን ውስጥ በአውሮፓውያኑ 1963 ንግግር ባደረገበት ወቅት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሰነዶቹ ከማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ነፍሰ ገዳይ ከአሰሳ ጀርባ "የኤፍቢአይ የውስጥ ማስታወሻዎች" እና "ከዚህ በፊት ያልታዩ የሲአይኤ መዛግብትን" ያካትታሉ ሲል የብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር ገልጿል።

ሰነዶቹን ይፋ የማድረጉ ሂደት ኤፍቢአይ፣ ፍትሕ መሥሪያ ቤት፣ ብሔራዊ መዛግብት እና ሲአይኤ በቅንጅት የተደረገ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፓሜላ ቦንዲ "የአሜሪካ ሕዝብ ከአገራችን ታላላቅ መሪዎች አንዱ ላይ አሰቃቂ ግድያ ከተፈፀመ ከዓመታት በኋላ መልስ ሊያገኝ ይገባዋል" ብለዋል።

ሁሉም የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ቤተሰቦች በሰነዶቹ ይፋ መሆን አልተበሳጩም።

የሲቪል መብቶች መሪውን "አጎቴ" ሲል የጠቀሰው አልቬዳ ኪንግ እንዳለው፤ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር ጋባርድ ግልፅነትን በተመለከተ የገቡትን ቃል በማክበራቸው አመስጋኝ ነኝ።በእሱ ሞት ማዘናችንን እየቀጠልን ቢሆንም የነዚህ ሰነዶች ይፋ መደረግ የአሜሪካ ሕዝብ የሚገባውን እውነት ለማግኘት ታሪካዊ እርምጃ ነው።"

የትራምፕ ተቺዎች የኪንግ ሰነዶች ይፋ የወጡት አስተዳደሩ እኤአ በ2019 በእስር ላይ እያለ ራሱን አጠፋ ከተባለው ተፅዕኖ ፈጣሪ የወሲብ ወንጀለኛ ጄፍሪ ኤፕስታይን ጋር በተያያዙ ፋይሎች ላይ ግልፅነት ጎድሎታል የሚል ክስ እየቀረበበት ባለበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል።

የሲቪል መብቶች መሪ አል ሻርፕተን የኪንግ ሰነዶች ይፋ የተደረጉት "ትራምፕን በኤፕስታይን ፋይሎች እና ከታማኝነታቸው ጋር በተያያዘ ያለውን ከፍተኛ ተቃውሞ ከመግለጽ ለማዘናጋት የተደረገ ከባድ ሙከራ" ነው ብለዋል።

ከመታሰሩ በፊት የኪንግ ገዳይ ጀምስ ኧርል ሬይ ከአገሩ ወደ ካናዳ፣ፖርቹጋል እና ዩናይትድ ኪንግደም በመሸሽ ባንክ ዘርፎ ነበር።

ወደ ሜምፊስ ግዛት ተላልፎ በ1969 የጥፋተኝነቱን ካመነ በኋላ የ99 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

በኋላም በጥላቻ ሴረኞች የተቀነባበረ መሆኑን በመግለጽ ጥፋተኝነቱን ለመካድ የሞከረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ቅጣቱ በፍርድ ቤቶች በደጋሚ ጸንቷል። ሬይ በ1998 በ70 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።