ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሞሮኮ በስፔን ላይ ድል ስትቀዳጅ፣ ሮናልዶን ተክቶ የገባው 3 ጎሎችን አስቆጠረ
ትናንት በተደረጉ የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች ያልተጠበቀ ውጤት ተመዝግቧል።
አፍሪካዊቷ ሞሮኮ የእግር ኳስ ኃያሏ ስፔንን በማሸነፍ የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀላቅላለች።
እአአ 1990 ላይ ካሜሮን፣ እአአ 2002 ላይ ሴኔጋል እንዲሁም እአአ 2010 ላይ ጋና ሩብ ፍጻሜን የተቀላቀሉ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ሲሆኑ ሞሮኮም ይህን ታሪክ መጋራት ችላለች።
ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ውድድር ያለ ጎል በመጠናቀቁ ወደ ተጨማሪ ሰዓት አምርተው ነበር።
ቡድኖቹ በተጨማሪ ሰዓትም ጎል ማስቆጠር ባለመቻላቸው በፍጹም ቅጣት ምት መለየት ግድ ሆኗል።
ስፔኖች የመጀመሪያዎቹን ሦስት ፍጹም ቅጣት ምቶች ስተዋል። ድንቅ ሆኖ ያመሸው የሞሮኮ ግብ ጠባቂ ያሲን ቦኖ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶችን ማዳን ችሏል።
ማድሪድ ተወልዶ ስፔን ያደገው ሞሮኳዊው አሽራፍ ሃኪሚ ወሳኟን ፍጹም ቅጣት ምት ወደ ጎል በመቀየር ስፔንን ከኳታር አሰናብቷታል።
ለዋንጫ ከተገመቱ አገራት መካከል አንዷ የነበረችውን ስፔን ያሸነፉት ሞሮኮዎች ከድላቸው በኋላ ብዙ አድናቆት እየደረሳቸው ይገኛል።
የሞሮኮ ንጉስ መሐመድ አምስተኛ ሳይቀሩ ስልክ አንስተው መላው ቡድኑን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ትናንት ምሽት በተካሄደው ሌላኛው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ፖርቹጋል ስዊዘርላንድን በሰፊ የጎል ልዩነት ማሸነፍ ችላለች።
ፖርቹጋል 6 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት ተጋጣሚዋን ብትረታም ትልቁ መነጋገሪያ ሆኖ ያመሸው የክርስቲያኖ ሮናልዶ በተቀያሪ ወንበር ላይ መቀመጥ ነው።
የፖርቹጋል አሠልጣኝ ፈርናንዶ ሳንቶስ ቡድናቸው ከስዊዘርላንድ ጋር በነበረው ጨዋታ ሮናልዶን በተቀያሪ ወንበር ላይ አድርገው ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
በምድብ ድልድሉ ፖርቹጋል የመጨረሻውን ጨዋታ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ስታደርግ ሮናልዶ ተቀይሮ ሲወጣ ባሳየው ምልክት ደስተኛ እንዳልነበሩ አሠልጣኙ አልሸሸጉም።
ሮናልዶ የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ትልቅ ግጥሚያዎችን ሲያደርግ በተቀያሪ ወንበር ላይ ሆኖ ጨዋታ የተጀመረው እአአ 2008 ላይ ነበር።
በሮናልዶ ተተክቶ ሜዳ የገባው ጎንሳሎ ራሞስ ሦስት ጎሎችን አስቆጥሮ “ሃትሪክ” ሰርቷል።
የ21 ዓመቱ የቤነፊካ አጥቂ ራሞስ ሦስት ጎሎችን ያስቆጠረው በዚህ የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰለፍ ዕድል ካገኘ በኋላ ነው።
ሮናልዶ በ74ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ሲገባ በደጋፊዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ሮናልዶ ተቀይሮ ከገባ በኋላ በጨዋታ እንቅስቃሴ ጎል ቢያስቆጥርም ግቧ ከጨዋታ ውጪ ተብላ ተሽራለች።