በሕንድ መንግሥታዊ ስነ-ስርዓት ላይ ተሳታፊ የነበሩ 11 ሰዎች በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, PTI
በሕንድ መንግሥታዊ ስነ-ስርዓት ላይ ተሳታፊ የነበሩ 11 ሰዎች በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ሞቱ።
በሕንዷ ማሃራሽትራ ግዛት በአንድ የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል 11 ሰዎች በከፍተኛ ሙቀት ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
በመንግሥት የተዘጋጀው ስነ-ስርዓት ያለምንም ከለላ ሰፊ ገላጣማ ቦታ ላይ ለሰዓታት ተካሂዷል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን ብዙዎች በውሃ ጥም መሰቃየታቸውን እና ከሙቀት ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች ገጥመውናል ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።
ከሙምባይ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ናቪ ሙምባይ ከተማ ስነ ስርዓቱ ሲካሄድ የነበረው ሙቀት 38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነበር።
የጤና ባለሙያዎች ቀደም ብለው በዚህ ሞቃታማ ወቅት ሰዎች ከረፋዱ 5 ሰዓት እስከ ከሰዓት 10 ሰዓት ድረስ በቤት እንዲቆዩ ማሳሰቢያ ሲሰጡ ነበር።
በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ የተወሰዱ ምስሎች ተሳታፊዎች ያለ ምንም ጥላ በቀጥታ ጸሐይ እያገኛቸው ስነ-ስርዓቱን ሲከታተሉ አሳይቷል።
ባለስልጣናት ግን ለተሳታፊዎች ምግብ እና መጠጥ መቅረቡን እና የጤና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ደግሞ ግዜያዊ ክሊኒክ አቋቁመናል ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሳተፋቸውን እና ስነ-ስርዓቱ ለሦስት ሰዓታት መዝለቁን ዘግበዋል።
ተሳታፊዎች የውሃ ጥም፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ድካም ተሰምቶናል ያሉ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ግን ስነ-ስርዓት በአግባቡ አልተከናወነም፤ እንደውም በዚህ ሞቃታማ ወቅት መካሄድ አልነበረበትም ያሉ ሲሆን በክስተቱ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በዚህ ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ተሳታፊ ሆነው ነበር። የአገር ውስጥ ሚንስትሩ አሚት ሻህ እና ግዛቱን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ኃላፊዎች ተሳታፊ ነበሩ።
የግዛቷ አስተዳዳሪ ኢክናት ሺንዱ ክስተቱን “ያልተጠበቀ እና አሳዛኝ” ብለው ከገለጹት በኋላ ለእያንዳንዱ የሟች ቤተሰብ 500ሺህ ሩፒ (6ሺህ የአሜሪካ ዶላር) ካሳ ይሰጣል ብለዋል።
ወደ ሆስፒታል የተወሰዱትን ደግሞ ሕክምናቸው በመንግሥት ይሸፈናል የግዛት አስተዳዳሪው።












