በሊቢያ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የአገሪቱን ፓርላማ ወረሩ

ታትሟል

ተቃዋሚ ሰልፈኞች በምሥራቃዊቷ የሊቢያ ከተማ ቱብሩክ ውስጥ የሚገኘውን የአገሪቱን ፓርላማ ወረው ከፊል ሕንጻውን በእሳት ማቃጠላቸው ተዘገበ።

በበይነ መረብ ላይ የተሰራጩ ምስሎች ከፓርላማው ሕንጻ ውጪ የተሰባሰቡ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ጎማዎችን ሲያቃጥሉና ጥቁር ጭስ አካባቢውን ሲሸፍነው አሳይተዋል።

በተለያዩ የሊቢያ ከተሞችም የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥን፣ የዋጋ ንረትን እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን በመቃወም ሰልፎች ተካሂደዋል።

በሌላ ተቀናቃኝ ኃይል አስተዳደር ስር በምትገኘው በዋና ከተማዋ ትሪፖሊም ምርጫ እንዲደረግ የሚጠይቅ ሰልፍ ተደርጓል።

ጥያቄያቸውም በሊቢያ ተቋማት ላይ ለውጥ መደረግ አለበት በሚሉትና የአገሪቱ ጊዜያዊ የአንድነት መንግሥትን በሚመሩት አብዱል ሃሚድ ቢባህ ድጋፍ አግኝቷል።

ተቃውሞው የተከሰተው በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት በአገሪቱ ምርጫ እንዲካሄድ ለማስቻል ጄኔቫ ውስጥ ተካሂዶ እምብዛም ውጤታማ ያልሆነው ንግግር ከተከናወነ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

ሊቢያ ለረዥም ዓመታት የመሯት ኮሎኔል ሞአማር ጋዳፊ በሰሜን አትላንቲክ ጦር ኃይሎች ድጋፍ ከአሥር ዓመት በፊት ከሥልጣን ተወግድው ከተገደሉ በኋላ በቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

በነዳጅ ሃብት የበለጸገችው ሊቢያ ግጭት ውስጥ ከመግባቷ በፊት ዜጎቿ ነጻ ሕክምናን እና ትምህርትን በማግኘት በአፍሪካ በከፍተኛው የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኙ ነበር።

በአሁኑ ወቅት መንግሥታዊ ሥርዓቷ በእርስ በርስ ጦርነትና ክፍፍል ምክንያት በመንኮታኮቱ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ወደ አውሮፓ ለመሻገር ለሚፈልጉ ስደተኞች ዋነኛ መተላለፊያ መስመር ናት።

ለብልጽግናዋ ወሳኝ የነበረው ሰላሟ በመናጋቱ በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ ውስጥ ሳይቀር ተቀናቃኝ ኃይሎች የበላይነትን ለመያይዝ ተደጋጋሚ ውጊያ ያደርጋሉ።