በህንድ የተደፈረች ታዳጊ እርዳታ እየተማጸነች መንገድ ላይ ስትዞር መታየቱ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በህንድ አንዲት የተደፈረች ታዳጊ እርዳታን እየተማጸነች መንገድ ላይ ስትዞር የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱ ቁጣን ቀስቅሷል።
ይህች ታዳጊ አንድን ሰው እንዲረዳት ስትጠጋው በእጁ ሲያባርራት በቪዲዮው ላይ የሚታይ ሲሆን በበርካቶችም ላይ ቁጣን ፈጥሯል።
በማድያ ፕራዴሽ ግዛት ኡጃይን ከተማ ውስጥ ከሁለት ሰዓት በላይ በእግሯ የዞረችው ታዳጊ አንዳንድ ሰዎች እርዳታ እንዳደረጉላትም ፖሊስ ለኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ገልጿል።
ታዳጊዋ መደፈሯን በህክምና መረጋገጡንም አንድ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣን ተናግረዋል።
“ታዳጊዋ ጋር ተገናኝተዋል የተባሉ አምስት ሰዎች እየተጠየቁ ነው” ሲሉ የኡጃይን ፖሊስ ኃላፊ ሳቺን ሻርማ ለኤኤን አይ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ታዳጊዋ “የምትናገረው ነገር የተወዛገበና ስለምትገኝበትም ቦታ መረጃ መስጠት አቅቷት እንደነበር” ኃላፊው ተናግረዋል።
ፖሊስ እስካሁን የታዳጊዋን ትክክለኛ ዕድሜ አላረጋገጠም።
በዚህ ሳምንት ለዕይታ የበቃው አጭር ቪዲዮ በማህበረሰቡ እና በፖለቲከኞች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ውግዘት አስነስቷል።
ቪዲዮው ላይ ታዳጊዋ ደሟን እያዘራች መንገድ ላይ ስትሄድም ያሳያል።
አንድ ግለሰብ እንዲረዳት ብትጠጋውም በእጁ ሲያባርራትም ይታያል።
ታዳጊዋ እርዳታ ከማግኘቷ በፊት የመጣችበትን ዱካ ለመከተልም ከአካባቢው የተቀረጹ ሌሎች የሲሲቲቪ ቪዲዮዎችንም እየገመገመ እንደሆነም ፖሊስ ተናግሯል።
ታዳጊዋ ሳትና ከተሰኘት ከተማ እሁድ እለት መጥፋቷ የተነገረ ሲሆን የተገኘችውም በ700 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ነው።
ራህል ሻርማ የተሰኙ የሂንዱ የሃይማኖት አባት እንደረዷትም የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የሃይማኖት አባቱ ባገኟትም ወቅት ታዳጊዋ ደም እየፈሰሳት እንደነበር ተናግረዋል።
“መናገር አልቻለችም። አይኖቿ አብጠው ነበር” ሲሉም ራህል ሻርማ ለኤንዲቲቪ የዜና ጣቢያ ተናግረዋል።
“ከዚያ ምን እንደተፈጠረ ጠየቅኳት። ነገር ግን ትመልስልኝ የነበረው በማይገባኝ ቋንቋ ነበር። እስክርቢቶና ወረቀት ብሰጣትም ምንም መጻፍ አልቻለችም” በማለት ለሂንዱ ጋዜጣ ተናግረዋል።












