የሶማሌ ክልል ከ100 በላይ የአልሸባብ አባላትን እንደገደለ አስታወቀ

የአልሸባብ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ከሰሞኑ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ የገባውን የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ከ100 በላይ አባላት መገደላቸውን የሶማሌ ክልል ጸጥታ ምክር ቤት አስታወቀ።

ለሶስት ቀናት በተካሄደ ዘመቻ ከ100 በላይ የአልሻባብ ቡድን አባላት መገደላቸውንና ሙሉ በሙሉ መደምሰሳቻቸውን ምክር ቤቱ በትናንትናው ዕለት ሐምሌ 16፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

ከአምስት ቀናት በፊት አቶ በሚባለው ቦታ ወደ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ዘልቆ መግባቱን የገለጹት የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን መንግሥት ሸኔ ብሎ ከሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ለመገናኘትም አቅዶ ነበር ብሏል መግለጫው።

የአልሸባብ አባላት በኤልከሬ ወረዳ አልፈው ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ጋር ለመገናኘት ቢያቅዱም ያሰቡበት ቦታ እንዳልደረሱም ተነግሯል።

የታጣቂው ቡድን 13 ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል እንዲሁም ይዞት የገባው ትጥቅና ስንቅም ተማርኳል ተብሏል።

ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት በመፈጸም እምብዛም ታሪክ የሌለው አልሻበብ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ድንበር ተሻግሮ ከገባ በኋላ ከሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ጋር ከባድ ግጭት መካሄዱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አልሸባብ ከሰሞኑ በአዋሳኝ አካባቢዎች ከፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ በቡድኑ ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ምንጩን ጠቅሶ የዘገበው ሮይተርስ፣ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ከባድ መትረየሶችና ተሽከርካሪዎችን ከቡድኑ ታጣቂዎች መማረኩን ጨምሮ አመልክቷል።

በተመሳሳይ የአልሸባብ ወታደራዊ ዘመቻዎች ቃል አቀባይ ሁለት መንደሮችን መያዛቸውን፣ በርካታ የልዩ ፖሊስ አባላት መግደላቸውን እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን መማረካቸውን ለሮይተርስ ሲገልጽ፣ በቡድኑ ታጣቂዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ግን ከመናገር ተቆጥቧል። 

ለሶስት ቀናት በተካሄደው ወታደራዊ ኦፕሬሽን የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በከፍተኛ ሚና እንደተወጣ የገለጸው የሶማሌ ክልል ጸጥታ ምክር ቤት የሶማሌ ክልል ህዝብ በምግብ፣ በአልባሳት እንዲሁም ደም በመለገስ ከልዩ ኃይል ጎን ቆመዋል ብሏል።

በተጨማሪም የኦፕሬሽኑን ስኬት በተመለከተ መረጃዎች ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ የጸጥታ ምክር ቤቱ በተጨማሪ ገልጿል።

በተጨማሪም ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሰርገው በመግባት የሽብር ጥቃት  ሊፈጽሙ የነበሩ ናቸው የተባሉ ከ450 በላይ የተለያዩ ቡድኖች አባላት በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን  የፌደራል የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በትናንትናው ዕለት ሐምሌ 16/2014 ዓ.ም. አስታውቋል።

ከነዚህም ውስጥ የሶማሊያው አስላማዊ ቡድን አልሻባብ እና ዓለም አቀፉ የሽብር ቡድን አይኤስ 31 አባላት በአዲስ አበባ ውስጥ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም እና ትርምስ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል ከተባሉት 454 ተጠርጣሪዎች መካከል ይገኙበታል።

በሶማሊያ ውስጥ በሚፈጽማቸው ከባድ ጥቃቶች የሚታወቀው አስላማዊው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ፣ አልፎ አልፎ በጎረቤት አገር ኬንያ ውስጥም ጥቃት ሲፈጽም ይታወቃል።

ነገር ግን ከዓመታት በፊት ጀምሮ ሠራዊቷን ሶማሊያ ውስጥ አሰማርታ እየተዋጋችው ባለችው ኢትዮጵያ ላይ ቡድኑ ይህ ነው የሚባል ጥቃት ፈጽሞ አያውቅም።